ʺሀገራቸውን ሲመርጡ አጋዣቸውን ተሰጡ”

98
ʺሀገራቸውን ሲመርጡ አጋዣቸውን ተሰጡ”
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) መልካም ልብ መልካም ነገር ያስባል፣ መልካም አንደበት መልካም ነገር ይናገራል፣ መልካም እጅ መልካም ነገር ይሠራል፣ መልካም ጆሮ መልካም ነገር ይሰማል፣ መልካም ዓይን መልካም ነገር ያያል፣ መልካም ማሕጸንም መልካም ፍሬ ይዘራል፣ “እነሆ ልጆች የፈጣሪ ስጦታ ናቸው፣ የሆድም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው። በኃያል እጅ እንዳሉ ፍላጾች፣ የጐልማሳነት ልጆች እንዲሁ ናቸው። ከእነርሱ ዘንድ ምኞቱን የሚፈጽም ብፁዕ ሰው ነው፤ ጠላቶቻቸውን በአደባባይ በተናገሩ ጊዜ እርሱ አያፍርም” እንዳለ ሀገራቸውን ሲመርጡ አጋዣቸውን ተሰጡ፡፡
መፈጠሪያ፣ መኖሪያ፣ ዓለም ማያ የሆነቻቸውን ሀገራቸውን ይመርጡ ዘንድ ወጡ፡፡ ሀገር ባዘጋጄችው ድግስ ሀገራቸውን መረጡ፡፡ ሀገር ብቻ መርጠው አልተመለሱም፣ ረዳት፣ መደሰቻ አጋዣቸውን ተሰጡ እንጂ፡፡ ከቤታቸው ወደ ምርጫ ጣብያቸው ሲሄዱ ልጅ በማሕጸናቸው ይዘው አቀኑ፣ ከምርጫ ጣቢያቸው ወደቤታቸው ሲመለሱ ደግሞ የማሕጸናቸውን ፍሬ በጀርባቸው ይዘው ተመለሱ፡፡
ወይዘሮ ውባየሁ ወርቁ ይባላሉ፡፡ ነዋሪነታቸው በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ጓንጓ ወረዳ ነው፡፡ እርሳቸው የሚኖሩባት ቀበሌ ደግሞ ሉንፅ ደገራ ትባላለች፡፡ ወይዘሮ ውባየሁ ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫን ለመምረጥ ጓጉተዋል፡፡ በመረጡት መንግሥት እየተዳደሩ በማሕፀናቸው ያደረውን ልጅ በሰላም መገላገል ተመኝተዋል፡፡ ምኞታቸውን ይፈጽምላቸው ዘንድ ፈጣሪያቸውን ተማጽነዋል፡፡
የጓጉለት ቀን ደርሷል፡፡ የምርጫ ካርዳቸውን ይዘው ወደምርጫ ጣብያ ሄዱ፡፡ ስለ ሰላም፣ በሰላም ሀገራቸውን ለመምረጥ እየተጠባበቁ ነው፡፡ የምርጫ ጣብያቸው ወልደኋይታ መራጮች ወረፋ ይዘው ቆመውባታል፡፡ ወይዘሮ ውባየሁ በምርጫ ጣቢያው ሳሉ ያልጠበቁት ነገር ተሰማቸው፡፡ እነሆ የማሕጸናቸው ፍሬ የማሕጸን ዘመኔን ጨርሻለሁ፡፡ ዓለም ላያትም ጓጉቻለሁ አላቸው፡፡ መንገዱን መጥረግ ጀመረ፤ የምጥ ምልክት ታያቸው፡፡
ከወረፋ ቀድመው ይመርጡ ዘንድ ተሰጣቸው፡፡ ታላቅ እንግዳ ምድርን ላይ ዘንድ መጥቻለሁ ብሏቸዋልና የተቀየማቸው አልነበረም፡፡ ከወረፋ ቀድመው ቀዳሚዋ ሀገራቸውን መረጡ፡፡ ዓለምን ለማዬት የጓጓው የማሕጸን እንግዳ ፈጥኗል፡፡ ምጡ ጠበቀ፡፡ በስፍራው የነበሩ አስታባባሪዎች ወደጤና ጣብያ ይሄዱ ዘንድ አመቻቹ፡፡ ለአምቡላንስ ተደወለ፡፡ ወደ ሆስፒታል ይዛቸው ከነፈች፡፡ በቻግኒ ሆስፒታል አደረሷት፡፡
መልካሟ እናት ሴት ልጅ ተሰጣቸው፡፡ ለወራት በማሕጸናቸው የጠበቀላቸውን የአብራካቸው ክፋይ እያዩት ይጠብቅላቸው ዘንድ ልጃቸውን እንካችሁ አላቸው፡፡ ጌታቸውን አመሰገኑ ልጃቸውንም በፍቅር ታቀፉ፡፡ ማሕጸናቸው በሰላም ተዳብሷልና፡፡
ከጓንጓ ወረዳ ኮምዩኒኬሽን የተገኘ መረጃን ታርቆ ክንዴ እንዳዘጋጀው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article‹‹ምርጫዉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል›› የእነዋሪ ከተማ ምርጫ ክልል መራጮች
Next articleበሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ምርጫዉ በሰላም እየተከናወነ መኾኑን የመንዝ ማማ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡