
“የምርጫው የእስካሁን ሂደት በመልካም ሁኔታ እየተከናወነ ነው” የአፍሪካ ሕብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የምርጫው የእስካሁን ሂደት በመልካም ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ ገለጹ።
የአፍሪካ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ዛሬ ረፋዱ ላይ በአዲስ አበባ ምርጫ ክልል 21/22 ምርጫ ጣቢያ 4 እና 5 የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በአካል ተገኝቶ ታዝቧል።
የቡድኑ መሪ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ “ቡድኑ ከገባበት ቀን ጀምሮ የምርጫ ሂደቱን በተለያየ መልኩ ሲከታተል ነበር” ብለዋል።
የምርጫ ዝግጅቱን በተመለከተ አፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ ከኢትዮያ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተገናኝተው ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ከጸጥታ ተቋማት፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎችና ከሌሎች አካላት ጋር የምርጫውን ዝግጅት በተመለከተ መወያየታቸውንም አስታውሰዋል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፣ የጸጥታና የሎጅስቲክስ ችግሮች ቢስተዋሉም የምርጫ አስፈጻሚ አካላት ይህንን ተቋቁመው ምርጫውን ማስፈጸማቸውን ጠቁመዋል።
የምርጫው የእስካሁን ሂደትና የዛሬ ድምጽ አሰጣጥ በመልካም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የቡድኑ መሪ ገልጸዋል።
ቡድኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በአንዳንድ የክልል የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ሂደቱን በተመለከተ ተዘዋውሮ መመልከቱን ጠቁመው “የእስስካሁኑ ሂደት ጥሩ ደረጃ ላይ ነው” ብለዋል።
መራጩ ሕዝብ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአግባቡ በመረዳትና በመተግበር ምርጫ ቅደም ተከተላዊ ሥነ-ሥርዓቱን በተከተለ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
“መራጩ ከንጋት 12፡00 ጀምሮ ድምጽ መስጠት መጀመሩንም ተረድቻለው” ነው ያሉት፡፡
በምርጫው ተሳታፊ የሆኑ ከተለያዩ የፓርቲ አባላቶችን ማነጋገራቸው ገልጸው፤ እስካሁን ቅሬታ ያቀረበ ፓርቲ አለመኖሩን አረጋግጠዋል። ከዚህ በኋላም በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች በመዘዋወር የምርጫ ሂደቱን እንደሚታዘብ የአፍሪካኅብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን መግለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ