
‹‹የምርጫውን ውጤት መቀበል ለቃል መቆም ነው›› ርእሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 14/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ርእሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር በጎንደር ከተማ ድምጽ ሰጥተዋል፡፡ ድምጽ ከሰጡ በኋላ ለጋዜጠኞች ሀሳባቸውን የሰጡት ርእሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር ምርጫው በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ለመትከል ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዘንድሮው ምርጫ ዴሞክራሲን ከመትከል፣ ሕዝብንና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከማሳተፍ አንጻር ለየት ያለ ምርጫ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ሕዝብ የሚሰጠውን ድምጽ አክብረን ካሸነፍን ሕጋዊ የሆነ መንግሥት መሥርተን፣ በቀጣይ ጊዜ የጀመርናቸውን እቅዶች እና የገባናቸውን ቃሎች ለመተግበር እንሠራለን ብለዋል፡፡ ከተሸነፍን ደግሞ ተፎካካሪ ፓርቲ ሆነን ለቀጣይ ራሳችንን ብቁ አድርገን እንመጣለን ነው ያሉት፡፡ ርእሰ መስተዳድሩ የምርጫውን ውጤት መቀበል ለቃል መቆም ነውም ብለዋል፡፡
የምርጫ ካርድ ያወጣ ሁሉም ሰው ድምጹን መስጠት እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡
ሰላምን ለማናጋት የሚደረጉ ሙከራዎች ተቀባይነት እንደሌላቸውም ገልጸዋል፡፡ ኅበረተሰቡ ሰላምን ለሚያናጉ አካላት ተባባሪ መሆን እንደሌለበትም አሳስበዋል፡፡ ሁሉም ነገር የሚፈጸመው በምርጫ ቦርድ ነው፤ ቦርዱ የሚያወጣቸውን ውጤቶች ለመቀበል ራስን ዝግጁ ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡
ከምርጫ በኋላ ችግር ቢፈጠር እንኳን እየተወያዩ እንደሚፈቱት ነው የተናገሩት፡፡ በኢትዮጵያ ደካማ መንግሥት እንዲመሠረት የሚፈልጉ ኃይሎች ምርጫው እንዲካሄድ አይፈልጉም ነበር፤ ምርጫው መካሄድ ነበረበት የሚሉ ወዳጆችም ነበሩ፣ ሁሉንም አዳምጠናል፣ ምርጫውን አካሂደናል፣ ምርጫውን ስናካሂድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ትተክላች፣ ሰላሟን አረጋግጣ መቀጠል ትችላለች ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን የምታስጠብቅ ሀገር ናት ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚወስነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ ሌሎች ኃይሎች አይደሉም፣ ኢትዮጵያ እየመረጠች ነው፣ ዛሬ ኢትዮጵያ አሸንፋለች ብለዋል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ