የኢትዮ-ቴሌኮም የሰሜን ሰሜን ምዕራብ ሪጅን በጎንደር ከተማ ለሚገኙ ሁለት ትምህርት ቤቶች የደብተርና የልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ።

224

ባሕር ዳር፡ መስከረም 9/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮ-ቴሌኮም የሰሜን ሰሜን ምዕራብ ሪጅን በጎንደር ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል ለመሠረት 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና ለፃዲቁ ዮሐንስ አጠቃላይ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡

የሪጅኑ ኦፕሬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ወርቃለማሁ ዳኛቸው እንደተናገሩት 1 ሺህ 950 ደርዘን የሚጠጋ የመማሪያ ደብተር ድጋፍ ተደርጓል፤ ከዚህ ውስጥ ለመሠረት 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች 1ሺህ 894 ደርዘን ደብተሮች መሰጠታቸውን አስታውቀዋል። ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ኢትዮ-ቴሌኮም የሚያደርገው ድጋፍ አካል እንደሆነ ነው የገለጹት።

ዳይሬክተሩ እንደጠቀሱት የሪጂኑ ሠራተኞች ደግሞ በግል መነሳሳት ከ53 ሺህ 500 ብር በላይ በማሰባሰብ በፃዲቁ ዮሐንስ አጠቃላይ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ለሚገኙ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ድጋፍ አድርገዋል። በዚህም የራዲዮና ፍላሽ፣ ዳይፐርና ሞዴስ፣ ሶፍት፣ ሳሙና፣ የብሬል ወረቀት፣ ፎጣ እና የራዲዮ ቻርጀር ድጋፍ አድርገዋል። በዚህም 55 ማየት የተሳናቸው፣ 56 መስማት የተሳናቸውና 38 የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለለባቸው የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።

አብመድ ያነጋገራቸው ወላጆች፣ መምህራንና ርዕሰ መምህራን የተደረገላቸው እገዛ ለተሻለ የትምህርት ሥራ የሚያነሳሳና አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች መልካም መሆኑን ጠቅሰው ምስጋና አቅርበዋል።

ከዚህ ተሞክሮ በመውሰድም ሌሎች ተቋማት ለተማሪዎችና ለትምህርት ቤቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ዘጋቢ- ፍፁምያለምብርሃን ገብሩ -ከጎንደር

Previous articleየአባይ ድልድይ ግንባታ ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት
Next articleኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ነዋይ ፍሰትን በመሳብ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራ ቀዳሚ መሆኗ ተገለጸ፡፡