
‹‹ምርጫው የኢትዮጵያን ሰርግ፣ የልጅህን ሰርግ የምታዬበት የሚመስል ድባብ ነው ያለው›› ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክበረት
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 14/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) በ6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በግላቸው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩት ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል 28 የምርጫ ጣብያ 06 ድምጻቸውን ሰጥተዋል፡፡
ድምጻቸውን ከሰጡ በኋላ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የተለያዩ ምርጫ ጣብያዎችን የማዬት እድል ነበረኝ ደስ የሚል ድባብ አለው ብለዋል፡፡ ከ11 ሠዓት በፊት መራጮች የመጡባቸው የምርጫ ቦታዎችን አይቻለሁም ነው ያሉት፡፡ አንዳንድ ቦታ የምርጫ አስፈጻሚዎቹና ታዛቢዎቹ ከሕዝቡ በኋላ መምጣታቸውንም ገልጸዋል፡፡ የሕዝቡ ጉጉት መልካም መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የሕዝብ የመምረጥ ፍላጎት ከአሁን በፊት በተደረጉ ምርጫዎች በ1997 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ማዬታቸውንም አስታውሰዋል፡፡ መራጮች በዛሬው ምርጫ ዝናብ ተቋቁመው ለምርጫ መውጣታቸውንም ተናግረዋል፡፡ በምርጫ ሂደቱ አንዳንድ ችግሮች ሲያጋጥሙም ከምርጫ ቦርድ ሰዎች ጋር እየተነጋገርን እየፈታናቸው ነው፣ ይህም ጥሩ የሚባል ነው ብለዋል፡፡ የምርጫ ቦርድ ሰዎችም ቀናና ፈጣን ምላሽ የሚሰጡ ስለመሆናቸውም ገልጸዋል፡፡
‹‹ምርጫው የኢትዮጵያን ሰርግ፣ የልጅህን ሰርግ የምታዬበት የሚመስል ድባብ ነው ያለው›› ብለዋል ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክበረት ፡፡
ካርድ ማውጣት የመጀመሪያው ሂደት ነው፣ ዋናውና ትልቁ ነገር ደግሞ በካርድህ የምትፈልገውን ነገር መወሰን መቻል ነው፣ የአንተ ካርድ ድምር ውጤት ነው መንግሥት የሚመሰርተው፣ ሶስት አይነት ጉዳት እንዳንጎዳ ወጥተን መምረጥ አለብን ብለዋል፡፡ መምረጥ ካልቻልን ለልጆች መጥፎ አርዓያ ነው የምናስቀምጠው፤ በራሳችን ማምጣት የምንችለውን ለውጥ ለሌላ ነው አሳልፈን የምንሰጠው፣ ባልመረጥነው መንግሥት ነው የምንተዳደረው ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ሶስቱም እድሎች በራስ ካርድ ላይ የሚወሰኑ ከሆነ ወጥቶ መምረጥ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡ ለሀገር የሚከፈል ዋጋ ስለሆነ ማንኛውንም ችግር ተቋቁሞ መምረጥ ይገባልም ብለዋል፡፡ እኛ በሰላም እንድንሰለፍ ሕይወቱን እየሰዋ በየዳር ድንበሩ ሠራዊት አለ፣ እርሱ ሕይወቱን ነው የሚሰዋው፣ እኛ ትንሽ ብንቆም፣ ፀሐይ ቢመታን፣ ቢደክመን፣ ለሀገር እንደሚከፈል መስዋዕትነት ብንቆጥር መልካም ነውም ብለዋል፡፡
እኛ ኢትዮጵያን ለመዳር የቆምን ሰዎች ነን፣ ሳይደከምን፣ ሳይሰለቸን በምንም መልኩ የእኔ ደምጽ ሳይገባ የምርጫ ፀሐይ መግባት የለባትም ብለን መወሰን ይገባልም ነው ያሉት፡፡ የኢትዮጵያ ጠላቶችን የምናሸንፈው በካርድ ነው ያሉት ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ከምርጫ መቅረት ከዓድዋ ዘመቻ እንደቀረን እንቁጠረው፣ ካርድ አውጥቶ ሳይመርጡ መቅረት፣ ዓድዋ ለመዝመት መሳሪያ ከተረከቡ በኋላ ሳይዘምቱ እንደመቅረት ነው ብልዋል፡፡
የፀጥታ ኃይሉና ሕዝቡ በቅንጅት ሰላሙን እንዲጠብቁ አሳስበዋል፤ በራስ ጉዳይ አይገባኝም ካሉ ማንም አይገባም ነው ያሉት፡፡ አጀማመሩ መልካም በመሆኑ ፍጻሜውም ሰላማዊ እንደሚሆን ያላቸውን እመነት ነው የተናገሩት፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ