በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልደታ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ለቀጣይ 5 ዓመታት የሚመራቸውን መሪ መምረጥ ጀምረዋል።

150
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልደታ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ለቀጣይ 5 ዓመታት የሚመራቸውን መሪ መምረጥ ጀምረዋል።
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 14/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከማለዳው 11:30 ጀምሮ መራጩ ሕዝብ በየምርጫ ጣቢያዎቹ በመገኘት የኮቪድ-19ን ፕሮቶኮል በጠበቀ መልኩ ድምጻቸውን ይሆነኛል ላሉት የፖለቲካ ፓርቲ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እየሰጡ ነው።
ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በ9 ክፍለ ከተሞች በእያንዳንዱ 14 እጩዎች በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ደግሞ 12 እጩዎች በአጠቃላይ 138 ወንበሮች ለከተማው ምክር ቤት የቀረቡ ሲሆን ከተማዋን ለሕዝብ እንደራሴዎች ለሚወክሉት ደግሞ 23 ወንበሮች ለውድድር ተዘጋጅተዋል፡፡
እስከአሁን ያለው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ዴሞክራሲያዊ መንገድን በተከተለ መልኩ የቀረቡት 8ቱም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎች እና ታዛቢዎች ባሉበት የድምፅ አሰጣጥ ሥነ ስርዓቱ ከጠዋቱ 12፡00 ጀምሮ እየተካሄደ ነው፡፡
በልደታ ክፍለ ከተማ በ2 የምርጫ ክልሎች በ113 የምርጫ ጣቢያዎች 85 ሺህ 728 መራጮች ካርድ ወስደዋል። በምርጫ ክልል 3 ስር ወረዳ 5፣ 7፣ 9 እና ወረዳ 8 በከፊል እንዲሁም በምርጫ ክልል 4 ስር ደግሞ ወረዳ 3 እና ወረዳ 4 እንዲሁም ወረዳ 8 በከፊል ተካተዋል።
በእያንዳንዱ ጣቢያ 5 የምርጫ አስፈጻሚዎች የተመደቡ ሲሆን አጠቃላይ በልደታ ክፍለ ከተማ ባሉ 113 የምርጫ ጣቢያዎች 565 የምርጫ አስፈጻሚዎች ተመድበዋል።
አሚኮ የሚገኝበት ልደታ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል 3 ምርጫ ጣቢያ 32 ውስጥ የሚገኙ 4 የምርጫ ጣቢያዎች እንዲሁም በወረዳ 7 ምርጫ ጣቢያ ለመራጮች ምቹ ሆነው መራጮች ድምጽ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
ድምፅ ለሚሰጡ መራጮችም ድምፅ የሚሰጡበትን ቦታ እንዲያውቁና ስለድምፅ አሰጣጡ አስፈላጊው ገለፃም ሲደረግ ተመልክተናል፡፡
በድምፅ መስጫ ጣቢያዎች የፀጥታ አስከባሪዎች በበቂ ሁኔታ ተሰማርተዋል፡፡
ለድምፅ አሰጣጡ ሂደት የሚያስፈልጉ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች እና ሌሎች ቁሳቁስ ተሟልተው ተመልክተናል፡፡ በምርጫ ሂደቱ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች በመራጩ ቁጥር ልክ መሆናቸውን የሰነድ ርክክብ፣ የድምፅ መስጫ ሳጥኖች ምንም አይነት ነገር በውስጣቸው አለመኖሩ የተረጋገጠበት እና ቁልፎችን በእማኞች ፊት በመፍታት እና በቀረበው ሰነድ ላይ በመፈራረም ተረካክበው ምርጫውን አስጀምረዋል።
ሁሉም አስፈጻሚዎች፣ ታዛቢዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን በተገኙበት ቁሳቁስን ከፍተው በማረጋገጥ እና የቀረበውን የስምምነት ሰነድ በመፈራረም ምርጫውን አስጀምረዋል። ለመራጩም ስለድምፅ አሰጣጡ ገለጻ እየተደረገ ነው፡፡
የድምፅ መስጫ ወረቀት አጠቃቀም፣ አንድ መራጭ የሚመርጠው ዕጩ ብዛት፣ የመወዳደሪያ ምልክቶቻቸው ደግሞ በትኩረት ገለጻ ሲሰጥ ተመልክተናል፡፡ ምቹ እና የመራጩን ነጻነት የማይነሳ የሚስጥር ድምፅ መስጫ ክፍል ተዘጋጅቷል። ለአካል ጉዳተኞች፣ለአዛውንቶችና የጤና ችግር ላለባቸው ቅድሚያ እየተሰጠም ይገኛል።
በክፍለ ከተማው 8 የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝብን ይሁንታ በካርድ ለማግኘት እየተፎካከሩ ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ1 ሚሊዮን 8 መቶ ሺህ በላይ ነዋሪዎች የምርጫ ካርድ የወሰዱ ሲሆን በልደታ ክፍለ ከተማ ደግሞ ከ78 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ካርድ ወስደዋል። በ2 የምርጫ ክልሎች ሥር 113 የምርጫ ጣቢያዎችም ለመራጮች ዝግጅ ሆነው ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ እያስተናገዱ ነው።
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፋንታሁን-ከልደታ ክፍለ ከተማ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበጉባላፍቶ ምርጫ ክልል ደብረ ገሊላ ምርጫ ጣቢያ ድምጽ መስጠት ተጀምሯል፡፡
Next articleበኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙ 8 የምርጫ ክልሎች 805 የምርጫ ጣቢያዎች አሉ። ከ ስምንቱ የምርጫ ክልሎች አንዱ በሆነው ግራርጃርሶ የምርጫ ክልል 64 የምርጫ ጣቢያዎች ይገኛሉ።