ሰኔ የእርሻ ሥራ የሚከወንበት የክረምት ወቅት ቢኾንም ከሀገር አይበልጥም እና ምርጫውን አስቀድመው ወደ እርሻ ሥራቸው እንደሚመለሱ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡

145

ሰኔ የእርሻ ሥራ የሚከወንበት የክረምት ወቅት ቢኾንም ከሀገር አይበልጥም እና ምርጫውን አስቀድመው ወደ እርሻ ሥራቸው
እንደሚመለሱ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 13/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የመራጭነት መብታቸውን ተጠቅመው የሚወክላቸውን ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን
በአማራ ክልል በተለያየ አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ነገ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡
መራጮችም መብታቸውን ተጠቅመው ለመምረጥ የምርጫ ቀኑን እየተጠባበቁ ነው፡፡
አርሶ አደር ጥላሁን ክንዴ የቡሬ ዙሪያ ወረዳ አለፋባሲ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደር ጥላሁን በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ
የሚወክላቸውን ፓርቲ ለመምረጥ የመራጭነት ካርድ አውጥተው የምርጫ ቀኑን እየተጠባበቁ ነው፡፡ አርሶ አደር ጥላሁን ካርድ
ማውጣት ብቻ ሳይኾን ካርዱን በመጠቀም የሚፈልጉትን የፖለቲካ ፓርቲ እንደሚመርጡም ነገረውናል፡፡
ሰኔ የእርሻ ሥራ የሚከወንበት የክረምት ወቅት ቢኾንም ከሀገር አይበልጥም እና ምርጫውን እንደሚያስቅድሙ አርሶ አደር
ጥላሁን ከአሚኮ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደር ጥላሁን በአካባቢያቸው የሚኖር እና እድሜው ከ18
ዓመት በላይ የኾነ ማንኛውም ሰው የወሰደውን የመራጭነት ካርድ በዕለቱ በመጠቀም የዜግነት ግዴታውን መወጣት
እንዳለበትም መክረዋል፡፡
“እኔም ለሀገሬ የድርሻዬን ለማበርከት የወሰድኩትን ካርድ ለመጠቀም እየተጠባበኩ ነው ብለዋል፡፡ ምርጫው በሰላም
እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደር ተገኘ አሠፋ በደብረ ኤልያስ ወረዳ የግዳድ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ በሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ የምርጫ
ካርድ ወስደዋል፡፡ አርሶ አደር ተገኘ ወቅቱ የእርሻ ሥራ የሚከወንበት ቢኾንም ምርጫው ለቀጣይ ሕይወታቸው ወሳኝነት ስላለው
ምርጫውን እንደሚያስቀድሙ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ ገልጸዋል፡፡
አርሶ አደር ተገኘ የሥራ ጊዜያቸው እንዳይባክን ቀድመው በመምረጥ ወደ እርሻ ሥራቸው ለመመለስ ማቀዳቸውንም ነግረውናል፡፡
“የእኔን ራዕይ ሊያሳካ የሚችለውን ፓርቲ ለመምረጥ ካርዴ ዋጋ አላት” ያሉት አርሶ አደር ተገኘ ሁሉም አርሶ አደሮች የተሠጣቸውን
እድል መጠቀም እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ ምርጫው የተረጋጋ እና ሰላማዊ በኾነ መንገድ እንዲካሄድ ሁሉም የድርሻውን
መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
አርሶ አደር ምስጋናው መላሽ በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደር ምስጋናው በ6ኛው
ሀገራዊ ምርጫ ድምጽ ለመስጠት ካርድ አውጥተዋል፡፡ አርሶ አደሩ ያወጡትን ካርድ በምርጫው ዕለት በመጠቀም
ኀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደር ምስጋናው ድምጽ የሚሠጥበትን ቀን በጉጉት
እየተጠባበቁ መኾኑንም ነግረውናል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብ የወሰደውን የምርጫ ካርድ በዕለቱ በመጠቀም ኀላፊነቱን
እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአጣዬና አካባቢው ተጎጂ ለሆኑ ወገኖች ከ8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ገለጸ፡፡
Next articleበእስቴ አንድ ምርጫ ክልል ምርጫ ጣቢያ ሁለት ድምጽ መስጠት ተጀምሯል፡፡