የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአጣዬና አካባቢው ተጎጂ ለሆኑ ወገኖች ከ8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ገለጸ፡፡

214
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአጣዬና አካባቢው ተጎጂ ለሆኑ ወገኖች ከ8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 11/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአጣዬና አካባቢው ቡድን አዋቅሮና ችግሮችን በጥናት እየለየ ተከታታይ የድጋፍ ሥራዎችን በማከናውን ላይ እንደሚገኝ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ባዩ ጌታሁን ተናግረዋል፡፡ ከአሁን ቀደም ለተጎጂዎቹ ምግቦችን፣ የምግብ ማብሰያዎችን፣ መመገቢያዎችን ለምግብ ዝግጅት የሚያገለግሉ የመኝታ ቁሳቁሶችንና ልዩ ልዩ አልባሳትን በማቅረብ ድጋፍ አድርጓል ብለዋል፡፡
የኒቨርስቲው በአራተኛ ዙር ድጋፉ የዩኒቨርሲቲውን ሠራተኞች፣ መምህራንና ተማሪዎችን በማስተባበር ልዩ ልዩ አልባሳትና ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በማሰባሰብ በተወካዮች በኩል አስረክኗል ነው ያሉት፡፡
የአጣዬ ከተማን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ሁሉ ቀፍ ጥረት የክልሉንና የዞኑን መንግሥት ለማገዝ በዩኒቨርሲቲው ተከታታይ የድጋፍ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ለመንግሥት ተቋማት ሥራ ማስጀመሪያ የሚሆኑ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ 100 ዴስክ ቶፕ ኮምፒውተሮችን፣ ከ600 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ አራት ሺህ ደስታ ወረቀቶችንና ግምቱ ከ130 ሺህ ብር በላይ የሚሆን ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ 22 አይነት መድኃኒቶችን በማጓጓዝ ለአጣዬ ከተማ ከንቲባ ማስረከባቸውን ተናግረዋል፡፡
የአሁኑ ድጋፍ በቁሳቁስ ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም በጥሬ ገንዘብ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ በድምሩ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ ለአራት ጊዜ በተደረጉ ድጋፎች በቁሳቁስና በጥሬ ገንዘብ ከ8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ድጋፍ መደረጉን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
የአጣዬ ከተማ ዋና ከንቲባ አቶ አገኘሁ መክቴ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአጣዬና አካባቢው የደረሰውን ጉዳት ግምት ውስጥ በመክተት በጥናት ላይ የተመሰረቱ ድጋፎችን በማድረግ ፈጥኖ ከሕዝቡ ጎን የቆመ የሕዝብ አገልጋይነቱን ያስመሰከረ ተቋም ነው ብለዋል፡፡ ዛሬ የተደረጉት ድጋፎችም አጣዬ ከተማን መልሶ ለማደራጀትና ጉዳት የደረሰባቸውን አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥራ ለማስጀመር እንደሚውሉም ጠቁመዋል፡፡
የዞኑ የምግብ ዋስትና እና አደጋ መከላከል ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወርቃለማው ኮስትሬ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በአጣዬና አካባቢው ማኅበረሰብ ላይ ለደረሰው ጉዳት ፈጣን ምላሽ የሰጠና ግንባር ቀደም መሆን የቻለ ተቋም ነው ብለዋል፡፡ ከገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲውን ተሸከርካሪዎች በመመደብ ከየአቅጣጫው ለሚደረጉ ድጋፎች የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት እገዛ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ሕብረት ምክትል ፕሬዚዳንትና የ3ኛ ዓመት የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪ ያሬድ ብርሃነ የዩኒቨርሲቲውን ማኅበረሰብ በማስተባበር ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ሲያሰባስቡ እንደቆዩ ተናግሯል፡፡የሕብረቱ አባላት በዩኒቨርሲቲው የተሰጣቸውን ተልእኮ በአግባቡ እየተወጡ እንደሚገኙም ነው የገለጸው፡፡
በቀጣይም አጣዬ ከተማን ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ውስጥ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተጨማሪ ሥራዎችን ለማከናወን ዝግጁ መሆናቸውን መግለጹን ከዩኒቨርስቲው የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየምሁራን ሚና ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚል የበይነመረብ ምክከር እየተካሄደ ነው፡፡
Next articleሰኔ የእርሻ ሥራ የሚከወንበት የክረምት ወቅት ቢኾንም ከሀገር አይበልጥም እና ምርጫውን አስቀድመው ወደ እርሻ ሥራቸው እንደሚመለሱ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡