የምሁራን ሚና ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚል የበይነመረብ ምክከር እየተካሄደ ነው፡፡

110
የምሁራን ሚና ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚል የበይነመረብ ምክከር እየተካሄደ ነው፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 11/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ውይይቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው። በዚህም ከሁሉም ዩኒቨርሲቲ የሥራ ኀላፊዎች እና የዩኒርቨሲቲ ማኅበረሰብ አካላት እየተሳተፉ ነው። የህዳሴ ግድብን ተከትሎ እየደረሰ የሚገኘውን ጫና ለመመከት ያስችላል የተባለው የዲጅታል ዲፕሎማሲውን ለማጠናከር ያለመ “የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማእከል” ተቋቁሟል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዳሉት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማእከል ኹሉም ዜጋ ዲፕሎማት ነው የሚለውን ሐሳብ ያጠናክራል። ኹሉም ኢትዮጵያውያን ህልማቸውን እውን ለማድረግ እውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውን እና ሃብታቸውን አስተባበረው ግድቡን እውን ሊያደረጉ እየተጉ ይገኛሉ ብለዋል። ኢትዮጵያውያን የዚህን ፍሬ ለማየት ወደተራራው እየዘለቁ ባሉበት ወቅት የኢትዮጵያን እድገት የማይፈልጉ አካላት ከዚህ ለመመለስ የሐሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ግብጽ ኢትዮጵያውያን ፍሬያቸውን እንዳያዩ ያለ የሌለ አቅሟን እየተጠቀመች ትገኛለች ያሉት አቶ ደመቀ ይህ ማእከልም የግብጽ እና መሰሎቿን ሴራ ለመቋቋም ምሁራኖችን ከተማሪዎች ጋር ለማቀናጀት ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነው ብለዋል።
ማእከሉ የበሰሉ ኢትዮጵያዊ ዲፕሊማቶችን ለማፍራትም ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡
የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ እንዳሉት ምሁራን ለሀገራቸው የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እያደገ መጥቷል፤ አሁንም ይህንን ሚና በማሳደግ ኢትዮጵያ እና አፍሪካን የማንቃት ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጅ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሽ በቀለ የሀገሪቱን የኃይል፣ የመስኖ እና የውኃ ሃብት አቅም በተመለከት የጽሁፍ ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡ አሁን ላይ ዝናብ በአስተማማኝ እና ከመደበኛ በላይ እያገኘን በመሆኑ የግድቡ ውኃ ሙሌቱ ያለምንም ችግር ይከናወናል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ዓባይ ለእናት ሀገሩ እርግማን ለጎረቤቶቹ ገጸ በረከት የሚሆንበት ዘመን አብቅቷል” ዶክተር ሙሉነሽ አበበ
Next articleየደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአጣዬና አካባቢው ተጎጂ ለሆኑ ወገኖች ከ8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ገለጸ፡፡