“ዓባይ ለእናት ሀገሩ እርግማን ለጎረቤቶቹ ገጸ በረከት የሚሆንበት ዘመን አብቅቷል” ዶክተር ሙሉነሽ አበበ

153
“ዓባይ ለእናት ሀገሩ እርግማን ለጎረቤቶቹ ገጸ በረከት የሚሆንበት ዘመን አብቅቷል” ዶክተር ሙሉነሽ አበበ
ባሕር ዳር: ሰኔ 11/2013 ዓ.ም (አሚኮ) “ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ገጸ በረከት ለዘላቂ ቀጣናዊ ትብብር” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምክክር እየተካሄደ ነው።
በምክክር መድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ደረጃ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ ዓባይ ለሀገሩ ጥቅም የሚሠጥበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡
“ለመወለድ ጊዜ አለው፤ ለመሞትም ጊዜ አለው፤ ለለቅሶ ጊዜ አለው፤ ለዘፈን ጊዜ አለው፤ ለትብብርም ጊዜ አለው፤ ለፉክክርም ጊዜ አለው፤ ለኹሉም ጊዜ አለው እንደተባለ ዓባይ ለሀገሩ እርግማን ለጎረቤቶቹ ገጸ በረከት የሚሆንበት ጊዜ አብቅቷል” ነው ያሉት።
ዓባይ ለእናት ሀገሩ፣ ለጎረቤቶቹም ልቦና ከሰጣቸው እና ከስግብግብነት ከወጡ ፍትሕና እውነትን ከተቀበሉ ለኹሉም ገጸ በረከት የሚሆንበት ወቅት አሁን መሆኑንም አስታውቀዋል።
በተለያዩ ዘመናት የተነሱ የኢትዮጵያ ነገሥታት ዓባይን ለመገደብ እና ለማልማት አስበውና ሞክረው እንደነበር ዶክተር ሙሉነሽ አስታውሰዋል፡፡ በቅዱስ ላልይበላ፣ በአፄ ዳዊት፣ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን መሞከሩን እና መታሰቡን ነው የጠቀሱት። በዚህ ሂደትም ኢትዮጵያ ጠንከር ስትል በገጸ በረከትና በዲፕሎማሲ ደከም ስትል በኃይል ለመውጋት በአብዛኛው ጊዜ የውስጥ ግጭት በመፍጠር ብዙ ሥራ እንደተሠራባትም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን በድህነት እና በጨለማ ውስጥ እንዲኖሩ መደረጉን ነው የገለጹት።
አሁን ላይ የሞት ጊዜ ሳይሆን የትንሣኤ፣ የጨለማ ጊዜ ሳይሆን የብርሃን ጊዜ መጥቷል፤ ዜማውም ተቀይሯል ብለዋል ዶክተር ሙሉነሽ። ለቀጣናው ሀገራት የሚያዋጣው ትብብርና ገጸ በረከቱን በጋራ መቋደስ ብቻ መሆኑንም ተናግረዋል። “እኔ እየበላሁ እናንተ ተራቡ፣ እኔ በብርሃን እየኖርኩ እናንተ በጨለማ ውስጥ ኑሩ” ማለት ማብቃቱንም አስገንዝበዋል፡፡ ይህ ደግሞ በተባበረ ክንድ እውን እንደሚሆን ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ለዘመናት የበይ ተመልካችና ተመፅዋች ሆና መቆየቷንም ተናግረዋል። በጋራ ማልማት ከተቻለ ዓባይ የቀጣናው በረከት እንደሚሆን ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያን እውነት በተለያዩ አጋጣሚዎች ማስረዳት እንደሚጠበቅም አሳስበዋል። ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ ዲፕሎማቶች እና ሌሎችም የበኩላቸውን እንዲወጡ ነው የጠየቁት። በዓባይ ላይ የነበረውን የውሸት ትርክት መቀየር እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።
የግብጽና የሱዳን ምሁራን እውነትን ሳይዙ ከሠሩት ሥራ ኢትዮጵያውያን እውነትን ይዘው የሠሩት እንደሚያንስ ነው ዶክተር ሙሉነሽ የገለጹት። የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ መሞገት የሚቻለው በዕውቀት፣ በጥበብ እና በጥናት መሆኑንም አመላክተዋል። በምክክር መድረኩ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በምሁራን ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሏል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“የወባ በሽታ ቅድመ መከላከል እና መቆጣጠር ሥራዎች እየተሠሩ ነው” የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት
Next articleየምሁራን ሚና ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚል የበይነመረብ ምክከር እየተካሄደ ነው፡፡