“የወባ በሽታ ቅድመ መከላከል እና መቆጣጠር ሥራዎች እየተሠሩ ነው” የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት

799
“የወባ በሽታ ቅድመ መከላከል እና መቆጣጠር ሥራዎች እየተሠሩ ነው” የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 11/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው ከመላ ሀገሪቱ መልከዓ ምድር 75 በመቶ የሚኾነው ለወባ በሽታ ስርጭት አመቺ ነው፡፡ 60 በመቶው የሚኾነው ሕዝብም በእነዚህ አካባቢዎች መኖሩ ለበሽታው ተጋላጭ አድርጎታል፡፡ በአማራ ክልልም የወባ ሥርጭቱ ከባለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነጻጸር መጨመሩን ከክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
የምእራብ አርማጭሆ ነዋሪ አቶ ዓለምነው ደምለው እንደነገሩን የአጎበር እና የኬሚካል አቅርቦቱ ዝቅተኛ ነው፣ የቀረበውም በወቅቱ ለማኅበረሰቡ አይደርስም፡፡ አቶ ዓለምነው የክረምቱን መግቢያ ተከትሎ የሚከሰተውን የወባ በሽታ ለመከላከል ቀድሞ የኬሚካል ርጭት መካሄድ ሲገባው በክረምቱ መውጫ ስለሚካሄድ ማኅበረሰቡ በወባ ተጋላጭ እንዲኾን አድርጎታል ነው ያሉት፡፡
ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ አቶ ፈረደ ጫኔ የአጎበር ሥርጭቱ ውስን በመኾኑ የወባ ስርጭቱን መከላከል አለመቻሉን አንስተዋል፡፡ በየጊዜው በወባ የሚያዙት ሰዎች ቁጥርም መጨመሩን ነው የገለጹት፡፡ ይሁን እንጅ ወባን ለመከላከል የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ እየተሠራ እንደኾነ አንስተዋል፡፡ መንግሥት አካባቢው ካለው የወባ ተጋላጭነት አንጻር በወቅቱ የአጎበር ስርጭት እና የኬሚካል ርጭት እንዲያከናውን እና በጤና ተቋማትም በቂ መድኃኒት እንዲያቀርብ ጠይቀዋል፡፡
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ ማስተዋል ወርቁ ወባ በክልሉ ዋና የኅብረተሰብ የጤና ጠንቅ ከሚባሉት ተላላፊ በሽታዎች ውስጥ አንዱ እንደኾነ አንስተዋል፡፡ ይህ ወቅትም ለወባ መተላለፍ አመች በመኾኑ የቅድመ መከላከል እና መቆጣጠር ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በ2010 ዓ.ም አጎበር ላሰራጩ 59 ወረዳዎች በዚህ ወቅት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን አጎበር እንደሚሰራጭ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን አጎበር ወረዳዎች ላይ ደርሷል፡፡
በመተማ፣ በገንዳ ውኃ እና በፎገራ ወረዳዎች ደግሞ ለተጠቃሚዎች ቀድሞ ተሰራጭቷል፡፡ ይሁን እንጅ በሌሎች አካባቢዎች በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ሥርጭቱ መዘግየቱን ነው ወይዘሮ ማስተዋል የገለጹት፡፡
የሀገር ውስጥ የጸረ ትንኝ ኬሚካል አምራች ፋብሪካ ማምረት በማቆሙ እና በበጀት ችግር ምክንያት ኬሚካሉን ከውጭ መግዛት አልተቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት በክልሉ ከፍተኛ የወባ ሥርጭት ባለባቸው ቋራ፣ መተማ፣ ምዕራብ አርማጭሆ፣ ጃዊ፣ ደራ እና ፎገራ ወረዳዎች ብቻ ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ ርጭት እንዲካሄድ ተደርጓል ብለዋል አስተባባሪዋ፡፡
የአልጋ አጎበር እና የጸረ ተባይ ኬሚካል ርጭት ከማድረግ በተጨማሪ ለወባ ትንኝ መራቢያ አመች የኾኑ ቦታዎችን ማጽዳት፣ ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስ እና የማዳፈን ሥራ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
የወባ ምልክት ከታየ ወደ አካባቢው የጤና ተቋማት በመሄድ ምርመራ ማካሄድ ይገባል፡፡ በሽታው ከተገኘም በባለሙያ የታዘዘውን መድኃኒት በትክክል መውሰድ እንደሚገባ ባለሙያዋ መክረዋል፡፡ የጤና ተቋማትም የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡
በአማራ ክልል በ2013 በጀት ዓመት እስከ ግንቦት መጨረሻ ከ480 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ ተጠቅተዋል፡፡ የወባ ሕሙማን ቁጥር ከ2012 ተመሳሳይ በጀት ዓመት ጋር ሲነፃጸር በ12 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“የአማራን ሕዝብ ወደ ፊት ማራመድ የሚቻለው የተማረ ወጣት ማፍራት ሲቻል ነው” የአማራ ክልል ርእስ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር
Next article“ዓባይ ለእናት ሀገሩ እርግማን ለጎረቤቶቹ ገጸ በረከት የሚሆንበት ዘመን አብቅቷል” ዶክተር ሙሉነሽ አበበ