
“የጥበብ ሀገሩ ኢትዮጵያ፤ የጥበብ አንደበት ግዕዝ ነው” ሊቃውንት
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የግዕዝ ቋንቋን እንደ አንድ የትምህርት አይነት ለማስተማር ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል። በምክክሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እና የእስልምና ሃይማኖት አባቶች፣ የቋንቋ መምህራን እና ተመራማሪዎች ተገኝተዋል። በምክክሩ የተገኙት ሊቃውንት እንዳሉት ግዕዝን በመደበኛ ትምህርት ለማካተት ብዙ ዘመናትን ሲታለም የቆዬ አሁን ላይ እውን ለማድረግ የተጀመረው ሥራ መልካም ተግባር ነው፤ የሀገርን ታሪክ ለማወቅ ግዕዝን ማወቅ ግዴታ መሆኑን አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ታሪክ ኹሉም በሚባል ደረጃ የተፃፈው በግዕዝ ቋንቋ መሆኑንም ገልጸዋል።
ግዕዝን ለዓመታት ወርውረን ጥለነዋል፣ ባንጥለው ኖሮ ሀገር የገጠማት ችግር አይገጥማትም ነበር፣ ነጮች ከወለዱት ስልጣኔ በፊት ግዕዝ ብዙ ነገሮችን ፈጥሯልም ብለዋል። ጥበብን ከራስ ሀገር መውሰድ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ግዕዝ ትልቅ አባት ነው፣ ከግዕዝ ትምህርት የበለጠ የዓለምን መንገድ የሚያሳዬን ዕውቀት የለም ነው ያሉት። ሀገር በቀል የሆነውን የመማር ማስተማር ዘዴ ማምጣት ተገቢ መሆኑንም አንስተዋል። ከሀገር ሀብት ላይ ዘግኖ መውሰድና ጥበብን ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል። በመንፈሳዊ ትምህርት ተምረው በግዕዝ ቋንቋ የላቀ ዕውቀት ያላቸውን ሰዎች እንዲያስተምሩ ማድረግ ተገቢ መሆኑንም ገልጸዋል።
“የጥበብ ሀገሩ የት ነው? ሲባል ኢትዮጵያ፤ የጥበብ አንደበትስ ማነው ሲባል ግዕዝ ነው” ይላሉ። ሥርዓተ ትምህርቱ ሲቀረፅ የቅኔ ሊቃውንትን መያዝ ካልተቻለ ትምህርቱን ለማስተማር እንደሚከብድም ተናግረዋል። በዘመናዊ የትምህርት ደረጃ የመምህራን ብቃት መለካት ግዕዝን በተፈለገው ልክ ሊያስሄደው እንደማይችልም ገልጸዋል። የአብነት ተማሪዎችን ከያዘ ቋንቋውን በተገቢው መንገድ ማስረፅ እንደሚቻልም አስታውቀዋል። ትምህርት ቢሮው ከቤተክህነት ጋር አብሮ መሥራት እንደሚገባውም አሳስበዋል።
ቋንቋውን ለማበልፀግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን መያዝ እንደሚገባ የተናገሩት የውይይቱ ተሳታፊዎች ቋንቋውን ከሃይማኖት ጋር አያይዞ ሊቃውንቱን ማግለል ቋንቋውን ይጎዳዋልም ብለዋል።
ግዕዝን መማር ጥበብን፣ ፍልስፍናን፣ መድኃኒት ቅመማን፣ ታሪክን እና ሥነጽሑፍም መማር መሆኑንም ተናግረዋል። ግዕዝን መማር ሃይማኖትን መቀየር አለመሆኑንም ሊታወቅ እንደሚገባ ነው የገለጹት። ግዕዝን ለመታደግና ለማበልፀግ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት መጀመር፣ አስተማሪዎቹ በቅኔ የተመረቁ ቢሆኑ የተሻለ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ቋንቋው ሃይማኖታዊ ሳይሆን መሣሪያ ነው፣ አረብኛውን ወደ እስልምና ግዕዝን ወደ ክርስትና ጥግ መስጠት ተገቢ አለመሆኑንም ገልጸዋል። ቋንቋውን ፊደል ከማስቆጠር ማስጀመር ይገባልም ተብሏል። የአስተምህሮ ስነ ዘዴው ከቤተክህነት ቢቀዳ የተሻለ እንደሚሆንም ተነስቷል።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግዕዝ ቋንቋ መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ጥበቡ አንተነህ
(ዶክተር) በ1985 ዓ.ም የዳሰሳ ጥናት ተደርጎ በኢትዮጵያ በግዕዝ ቋንቋ የተፃፉ ከ200 ሺህ በላይ የብራና መጻሕፍት እንደተጻፉ ጠቅሰዋል። ከእነዚህ መካከል የተሰነዱት 15 ሺህ ብቻ ናቸውም ነው ያሉት። ሌሎች አጥኚዎች ግን የጥቅል ጽሑፎችን ሳይጨምር አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ የብራና መጻሕፍት እንዳሉ መጥቀሳቸውን ነግረውናል። በየጊዜው የተለያዩ መጻሕፍት እየተገኙ በመሆናቸው ቁጥሩ ከዚህ በላይ ሊሄድ እንደሚችል ተነስቷል።
በውይይቱ ላይ ሐሳብ ያቀረቡት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዘኛ ትምህርት መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዐቢይ ግዛው ከጥበብ እንዳንርቅ ግዕዝን መማር ይገባል ነው ያሉት።
ተመራማሪው እንዳሉት የግዕዝ ቋንቋ ትንሣኤ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል ዕውቀት ትንሣኤ ነው፤ ኢትዮጵያ የጥበበኞችና የአዋቂዎች ሀገር ናት፤ ዓለም የሚያደንቀው ባለቤቱ የናቀው አያሌ ዕውቀት አለ። ኢትዮጵያ የራሷ ፍልስፍና፣ ኪነ ጥበብ፣ የመድኃኒት ቅመማ፣ ሥነጽሑፍና የተለያዩ ዘርፎች የመጠቀ ዕውቀት መገኛ ስለመሆኗም ገልጸዋል ፕሮፌሰሩ።
ተመራማሪው ኢትዮጵያ በሀገርኛ ዕውቀት የበለፀገች እና ወደር የማይገኝላት መሆኗንም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ሀብት ተመዝግቦ የሚገኘው በግዕዝ ቋንቋ መሆኑን አንስተዋል። ግዕዝን ሌሎች ሀገራት የራሳቸው ለማድረግ ጥረት እያደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያን ጥበብ ለማወቅና የዓለምን የተቃና ጥበብ ለማወቅ የውጭ ሀገራት ቋንቋውን እየተማሩና እያስተማሩት ነውም ብለዋል። ዓለም ያለችበት ዕውቀት ከኢትዮጵያ የተወሰደ ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ የግዕዝ መጻሕፍትን ምጡቅ ዕውቀት ለመረዳት ግዕዝን መረዳት ተገቢ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ዶክተር ጥበቡ ባዕዳን የኢትዮጵያውያንን ጥበብ ወስደው የራሳቸው እያስመሰሉ እንደሚያቀርቡም ገልጸዋል። የግዕዝ ቋንቋ ሀብት የማይነጥፍ፣ ውለታው የተረሳ፣ የግዕዝ ቋንቋ ለሚቀነቀው ዘመናዊነት ከሁሉም በላይ ጠቃሚ መሆኑንም አንስተዋል።
42 ዓመታትን በማስተማር ዘመናቸው ከግዕዝ ቋንቋ የመማር ማስተማር ዘዴ ከሁሉም የተሻለና ጥቅም ላይ ያልዋለ መሆኑን መረዳታቸውንም ፕሮፌሰር ጥበቡ ገልጸዋል። የግዕዝ ሀገሩ ኢትዮጵያ ናትም ብለዋል። ለኢትዮጵያ የሚልኩት ነገር ሁሉ ከኢትዮጵያውያን የተወሰደ ጥበብ መሆኑንም ገልጸዋል። ግዕዝ የኢትዮጵያውያን መሆኑን የሚያረጋግጥ ሥራ መሥራት ይገባል ብለዋል።
በዘመናዊ ትምህርት ፕሮፌሰር ከሆኑ ሰዎች በብዙ የሚልቁ የቤተክህነት ሰዎች ስላሉ እነርሱን መጠቀም እንደሚገባም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) የትምህርት ሥርዓቱ ሲወቀስበት የቆየው ትውልዱን በጥራትና በብቃት አለማስተማሩ መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ልሳነ ብዙ ሀገር ኾና ሳለ እርስ በርስ የሚጠራጠር ትውልድ የተፈጠረው አንደኛው ምክንያት የትምህርት ሥርዓቱ ችግር መሆኑን ተናግረዋል። ቋንቋን ማሳደግ ልዩነትን እያጠበበ፣ የጋራ ራዕይ፣ የጋራ ሀገር፣ የጋራ ታሪክና አንድ የልማት አጀንዳ እንዲኖር ያስችላል ብለዋል። ግዕዝን ማስተማር ሀገር በቀል መሠረታዊ ፅንሰ ሀሳብን ማወቅ መሆኑንም ተናግረዋል።
ዶክተር ይልቃል ግዕዝ ከቋንቋነት ባሻገር ዕውቀትን፣ መልካም ስብዕናን የሚላበሱበት ትልቅ መሣሪያ ነውም ብለዋል። ትምህርት ቢሮው የቤተክህነት ሊቃውንት፣ የዩኒቨርስቲ ምሁራንና ሌሎች የሚሰጡትን ሐሳብ ወስዶ ተግባራዊ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።
ትምህርቱን ለማስጀመር በሚደረጉ ሂደቶች ሌሎች ሥራዎች እንደሚኖሩም ተናግረዋል። የግዕዝን ትምህርት እውን ለማድረግ ትብብር እንደሚጠይቅም ገልጸዋል። በመስከረም ወር በተመረጡ ትምህርት ቤቶች እንደሚጀምርም ተገልጿል። ለመማሪያ መጻሕፍት ዝግጅት ሊቃውንት በጋራ እንዲሠሩም ዶክተር ይልቃል ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ