
የከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ መሬት ላይ ወርዶ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ተፈጻሚ እንዲሆንላቸው የቤት ማኅበራት መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ጠየቁ፡፡
ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ሕጋዊ የመኖሪያ ቤት ሥራ ማኅበራት ተደራጅተው ቦታ መጠባበቅ ከጀመሩ ከሰባት ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል፡፡ የተደራጁ ማኅበራት ብዛት ያላቸው መሆን፣ የከተማ አስተዳደሩ ፈፃሚ አካላት በየጊዜው መቀያየር እና የቦታ ጥበት ተደማምሮ ማኅበራቱ ጥያቄዎቻቸው ምላሽ ሳያገኙ ለረዥም ጊዜያት መቆየቱን ከተማ አስተዳደሩ ይጠቅሳል፡፡
ማኅበራቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በዝግ የባንክ ሂሳብ ማስቀመጣቸው እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የኑሮ ውድነት ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ እንዲሰጣቸው ከተማ አስተዳደሩን በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ቆይተዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩም የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ እና ለኹሉም ሕጋዊ የቤት ሥራ ማኅበራት የመኖሪያ ቦታ ለመስጠት መወሰኑን መግለጻችን ይታወሳል፡፡
በአዲስ ከሚሠራው የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ስትራቴጂክ ፕላን ጋር የተጣጣመ ቦታ እያፈላለገ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡ ለኹሉም ማኅበራት ቦታ ለመስጠት የሚያደረግው ጥረት ጊዜ መውሰዱን ተከትሎ ማኅበራቱ ቅሬታ አቅርበው ነበር ብሏል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ኮሚቴ የሕዝቡን ቅሬታ ተቀብሎ ትናንት ባደረገው ስብሰባ ለቀሪ ማኅበራት ቦታ በማፈላለግ ለኹሉም ማኅበራት ቦታውን ለመስጠት ውሳኔ ላይ መድረሱን አሳውቋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የደረሰበትን ውሳኔ አስመልክቶም ከማኅበራቱ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ማስረሻ በላይ የከተማ አስተዳደሩን ችግር ማኅበራቱ እንደሚረዱ ጠቅሰዋል።
የተደረሰው ስምምነት የጊዜ ገደብ የተቀመጠለት እና በመፍትሔ ሐሳብ ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል፡፡ ለኹሉም ማኅበራት ቦታ ለመስጠት መወሰኑን አድንቀዋል። በተለይም የብሎክ ልየታ ሲጠናቀቅ እና የካሳ ስሌት ግመታ ሲያልቅ በየጊዜው ሂደቱን ግልፅ ለማድረግ መወሰኑ እና ወደ ሥራ መገባቱ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ሂደቶች የተለየ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴው የማኅበር አባላቱን ስሜት ይዞ በተደጋጋሚ ከተማ አስተዳደሩን መጠየቁን ያወሳችው ኑሪያ ነጋ ዛሬ የተደረሰው ሥምምነት ተግባራዊ ሂደቶቹ ወዲያውኑ የተጀመሩ መሆኑ አስደሳች ነው ብላለች፡፡
10 በመቶ የቁጠባ ሂደቱ የሚገባበት ጊዜ መጀመሩ እና የካሳ ግመታው ስሌት እንደተጠናቀቀ ሂደቱን ለማሳወቅ ከንቲባ ኮሚቴው ስምምነት ላይ መድረሱም ጥሩ ጅማሮ መሆኑን ገልጻለች፡፡
የቦታ እጥረት በመኖሩ የተወሰኑ ማኅበራት ብሎካቸውን አውቀው የቦታ ክፍፍሉ ላይ የተወሰነ መዘግየት እንደሚኖር ተስማምተናል ያሉት የኮሚቴው አባላት የከተማ አስተዳደሩን ጥረት ከጎን በመሆን ለመደገፍ እንደተዘጋጁም ነው የነገሩን፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ ወደ መሬት ወርዶ እና በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ መሰረት ተፈፃሚ እንዲሆን የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎቹ ጠይቀዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩም በበኩሉ ከመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ጋር ውይይት አድርጎ ስምምነት ላይ መድረሱን ገልፆ በቀጣዮቹ ሳምንታት የካሳ ግምት እና የብሎክ ማሰር ተግባራትን ለማጠናቀቅ እንደሚሠራ አስታውቋል።
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ