
“አብሮነት ሲደራ በተከዜ ዳር ሑመራ”
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 05/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) ዘር ሳይቆጠር፣ ቋንቋ ሳይመረመር፣ ብሔር ሳይነገር የሰው ማንነቱ ሰውነቱ ብቻ ነበር። ሰው ከሰውነት ከወረደ ግርማ ይርቀዋል፣ ክብር ይተወዋል። ፈጣሪው አብዝቶም ይቀጠዋል። የሰው መለኪያውና ክብሩ ሰውነት ነው። ኢትዮጵያ በሰው ልጅ መገኛነት፣ በመንግሥት ምሥረታ ቀዳሚነት፣ በጥበብ አፍላቂነት፣ ሉዓላዊነትን በማስከበር፣ ለፍትሕና ለፍቅር በማበር ቀዳሚ ናት።
ፍትሕን ኢትዮጵያውያን ያስተምራሉ እንጂ ስለ ፍትሕ አይማሩም። ዘመናትን በተሻገረው የመንግሥትነት ታሪኳ፣ እልፍ ስኬቶች አሳክታለች፣ እልፍ ችግሮችን አልፋ ተጉዛለች፡፡
ትናንት ለዛሬ ፣ ዛሬ ለነገ ስንቅ እየኾነ ታሪክ እየተሠራ፣ ታሪክም እየተነገረና እየተዘከረ አልፏል። ኢትዮጵያውያን የተጋመደ የኑሮ ዘይቤያቸው፣ በማይሸነፈው ኃይላቸው፣ በሚያስደነግጠው ግርማቸው፣ በጠንካራው ኢትዮጵያዊነታቸው ዓለም ተገርሞባቸዋል። ቅን ልቦና ያለው ቆሞ ሲያጨበጭብላቸው፣ ክፉ ልቦና ያለው ደግሞ በፍቅራቸው እና በአንድነታቸው ሴራ ሸርቧል። በየዘመናቱ ጦር አዝምቷል። የቻለ በመጣበት እግሩ አምልጦ ሲመለስ፣ ያልቻለ በመጣበት ሲደመሰስ ኢትዮጵያ ራሷን አስከብራ ዘመናትን ተሻግራለች። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በዘመናት ቅብብሎሽ ታሪካቸው ከገጠማቸው ችግር አንዱ የአሸባሪው የሕወሓት ዘመን ነው ይላሉ።
በዚህ ዘመን አንድነት እንዲላላ፣ ወገን ከወገኑ እንዲጠላላ ተደርጓል። ክልል ተከልሎ አንድነት ተከፍሎ ዘር አይሎ ተስተዋለ። አንድነታቸው ለሚያበሳጫቸው የውጭና የውስጥ ኀይሎች ይህ ዘመን የፍስሃ ዘመን ነበር።
ለኢትዮጵያውያን ግን የመከራ ዘመን ኾነ። ኢትዮጵያውያን አንድነታቸው አኑሯቸዋል፣ አስከብሯቸዋል፣ አሸናፊ አድርጓቸዋልና ያን ዘመን አጥብቀው ጠሉት። ሥርዓቱ ፈፅሞ ከጠላቸው እነርሱም ፈፅመው ከጠሉት ኢትዮጵያውያን መካከል የወልቃይት ጠገዴ ነዋሪዎች ግንባር ቀደሞቹ ናቸው። የወልቃይት ጠገዴ የሥርዓት ይለወጥና ማንነት ይመለስ ጥያቄ የሕወሃትን የአገዛዝ ዘመን አሳጥሯል። ታሪክም ቀይሯል። አድራጊ ፈጣሪ የነበረው አሸባሪው ሕወሃት ዘመኑ አልቆበት፣ ለክቶ የሠራው የብርሃን ዘመን ጨልሞበት፣ ሕዝብ ፊቱን አዙሮበት ተሳዷል። ሀሳቡም የሀሳቡ ባለቤትም ተጠልቷል።
አሸባሪው ሕወሃት መለያየትን ከሰበከባት፣ የእብሪት ክንዱን ካሳየባት፣ ግፍና በደል ከፈፀመባት ከተማ ተገኝቻለሁ። የተከዜ ዳር ፈርጧ የበረሃዋ ገነት ሑመራ። በሑመራ የገባ ሁሉ ነዋሪ እንጂ እንግዳ አይኾንም። የመሸበት ያድራል፣ ፈቃዱ የኾነ ይሠራል። መኖር የከጀለ በነፃነት ኖሮ ልጅ ወልዶ ይድራል ይኩላል። ይህ የሑመራ ከተማ መገለጫ ነው። የሑመራ መልካም ታሪክ በሕወሃት ዘመን ተለወጠ። ተመርጠው የሚኖሩና ተመርጠው የሚሠሩ ሰዎች ይፈለጉ ጀመር። ፍቅርና አብሮነት መገለጫቸው የኾነው የሑመራ ነዋሪዎች የመከራውን ዘመን ይገፉት ጀመር። ያልኖሩበት ያላደጉበት፣ የማያውቁት ነገር በአሸባሪው ሕወሓት መጥቶባቸዋልና አዘኑ።
የመኖር መስፈርቱ ሰውነት በኾነባት ከተማ የነበረው ታሪክ ተመልሶ መጥቷል። የሕወሃት የአገዛዝ ዘመን ተጠናቆ፣ ሰውነት እና አብሮነት መነሻዋ የኾነችው ከተማ ሸክሟ ወረዶላታት። ተሰባስበው ሲጨዋወቱ፣ አክራሪ፣ ነፍጠኛ፣ የቀድሞውን ናፋቂ እያለ የሚከሳቸው፣ የሚያስራቸውና የሚያንገላታቸው የለም። ዘመን ገፍቶት፣ ጊዜ ጥሎት ጠፍቷልና።
በዚያች ከተማ በአንድ ቅፅር ግቢ ውስጥ የተሰባሰቡ ሰዎች አሉ። ክብ ሰርተው ተቀምጠዋል። በመካከላቸው ቡና ተፈልቶ ይታደላል፣ ሳቅና ጨዋታ ደርቶ የቡና ቁርስ ይበላል። ክብ ሰርተው በተቀመጡት ሰዎች ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾኑ አፍሪካዊያንም አሉበት። ቋንቋ ዘርና ሃይማኖት መስፍረታቸው አይደለም። የእነርሱ ፍቅር ልብን የሚያቀልጥ፣ አጥብቆ የሚያዋድድ ፍቅር ነው። በፍቅር የገመዷት አብሮነታቸው፣ በበረከት የተመላችው ሞሶባቸው እንዳትጎድል ብቻ ነው ምኞታቸው። በፍቅር ኑሩ ያላቸውን የአምላካቸውን ትእዛዝ አክብረዋልና፣ ሞሶባቸው አይጎድልም፣ ፍቅራቸው ቢፈተንም አይጠፋም የከፋውን ዘመን አልፈውታልና። አምላክ ይወዳቸዋል። የከፋውን ዘመን አሳልፏቸዋል። የሚመጣውን ዘመንም ያሳምርላቸዋል። ትዕዛዙን አክብረዋልና።
ፍቅራቸው አስቀናኝ፣ አንድነታቸው አስደመመኝ፣ እንደ ሳት የሚነደውን ሙቀት አብሮነታቸው አስረሳኝ። ከፍቅራቸው ወይን ልቀምስ፣ ከአንድነታቸው ዳቦ ልቆርስና ልቋደስ ወደድኩ።
ገብረ ሚካኤል ገብረ መድህን ይባላሉ። ትውልዳቸው ተንቤን ውስጥ ነው። ተከዜን ተሻግረው ወደ ሑመራ የዘለቁት የ14 ዓመት ልጅ እያሉ ነበር። እሳቸው የመጡበት ዘመን የፍቅር ዘመን ነበርና በፍቅር አድገው፣ በፍቅር ኖረው ወግ ማዕረግ አይተዋል። በዚችው ከተማ ዓመታትን በመልካም አሳልፈዋል። አሸባሪው ሕወሃት በለኮሰው እሳት እየተገረፈ ሲሸሽ ልትገደሉ ነው ቀያችሁን ለቃችሁ ውጡ ያለውን ጥሪ ገብረ ሚካኤል አልተቀበሉትም። ከልጅነት እድሜያቸው ጀምሮ በኖሩባት ከተማ መኖር፣ ከአሳደጋቸው ሕዝብ ጋር መቅረትን መረጡ እንጂ። “እኔም ቤተሰቦቸም ሰላም እየኖርን ነው፣ ጫና የለብኝም” ነው ያሉን። እርጋታቸው ደስ ይላል።
ህወሃትና ተከታዮቹ የትግራይ ተወላጆች ከሑመራ ውጡ ተብለዋል እያለ ያስወራል። የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ግን ማንነትን አስመለሰ፣ ሥርዓቱንም ገረሰሰ እንጂ አንተ ኑር አንተኛው ውጣ አላለም። ለዚህ ደግሞ እንኳንስ ኢትዮጵያዊው የትግራይ ሕዝብ ይቅርና የሑመራ ነዋሪው ሱዳናዊው አቡበክር መሃመድ ምስክር ነው። 19 ዓመታትን በሑመራ ተቀምጧል። አሁንም በሑመራ ኑሮውን እየመራ ነው። ክብ ሰርተው ቡና ሲጠጡ ነው ያገኘነው። “ሑመራ ውስጥ ከወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ጋር በፍቅርና በጋራ ነው የምንኖረው ሱዳናዊያን ብቻ ሳይኾኑ፣ ናይጄሪያውያን፣ ቻዳዊያን አሉ። ሁላችንም በፍቅር ነው የምንኖረው፣ ያጋጠመን ችግር የለም። ምንም አይነት ልዩነት የለም፣ እርዳታ እንኳን ሲመጣ፣ አይለዩንም እኩል ነው የሚሰጡን፣ የሚባለው ሁሉ ውሸት ነው ውጡ ያለን የለም” ነው ያለን።
ሡዳናዊው ሑመራን ሀገሩ የወልቃይት ጠገዴን ሕዝብ ደግሞ ወገኑ አድርጎ ነው የኖረው“ ፈርታችሁ የሄዳችሁ ሁሉ ተመለሱ፣ እኛ በሰላም እየኖርን ነው፣ ሰላማዊ ኖሯችሁን ቀጥሉ” ነበር ያለው። መስፈርቱ ፍቅር ሲኾን ዘር ቦታ አይኖረውም። የአንድ ሀገር ሕዝብ ይቅርና የተለያዩ ሀገራት ሕዝቦች በናፍቆት እየተቃቀፉ ይኖራሉ።
የኩናማ ተወላጁን በቀለ አባሳን አነጋገርናቸው ከወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ጋር አብረን ኖረናል። በፍቅርና በሰላም ነው የኖርነው። አሁንም ከወልቃይት ሕዝብ ጋር አብረን እየኖርን ነው፣ የደረሰብን ጫና የለም አሉን።
እውነታው ክብ ሰርተው በተቀመጡት ሰዎች ውስጥ የሚታየው ፍቅር፣ ያለው ሕብር ነው። ቡናዋ ባሰባሰበቻቸው ዙሪያ ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን ያገኛሉ። በቡናው ዙሪያ ፍቅር ክብር፣ ሕብር፣ አንድነት፣ ደግነት፣ ሰበዓዊነትና መልካምነት አለ። አብዝቶ ገረመኝ። በትንሹ የቀመስኩት ፍቅር ተመችቶኛል። ፍቅር ያሰባሰባቸውን በፍቅር ተሰናብተናቸዋል።
መሬት ላይ ያለው እውነት፣ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያለው ውሸት የተለያየ ፅንፍ ላይ እንዳሉ ተሰማኝ። ፍቅራቸውን እያሰብኩ፣ አብሮነታቸውን እያንሰላሰልኩ ወደፊት ገሰገስኩ። ወዳጄ እውነትን መሬት ላይ ተመልከታት። ሰውነት እና አላፊ ሥርዓት አንድ አይደሉም። አስተውለህ ተጓዝ፣ አነጣጥረህ ተመልከት፣ አስበህ ተናገር፣ አረጋግጠህ መስክር። የኢትዮጵያውያን ፍቅር በችግር የተፈተ ነውና ኢትዮጵያዊነታቸው፣ አንድነታቸውና አብሮነታቸው ለዘላለም ይኖራል። ዘመንን ይዋጁታል እንጂ ዘመን አይዋጃቸውም። መጥፎ ሥርዓትን ከሰውነት ጋር ይለዩታል እንጂ መጥፎ ሥርዓት ከሰውነት አይለያቸውም። ለምን ካሉ ከሁሉም የሚበልጠውን ፍቅርን ይዘዋልና። ፍቅራችሁ ይብዛ።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ