
“በሞትን አትግፉን፣ ብትችሉ ካሳ ባትችሉ ግን ዳግም ግፍ በቃን” የካድራወንዝ ከተማ ነዋሪዎች
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 04/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ በግፍ የጨፈጨፋቸው የካድራወንዝ (ማይካድራ) ከተማ ነዋሪዎች የትህነግን ግፍ በማውገዝና የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም ሰልፍ አካሂደዋል። የግፍ ፅዋ የፈሰሰባት፣ የንጹሃን ደም የተደፋባት፣ የጨካኞች የመጨረሻው የጭካኔ ጥግ የታየባት፣ እናት የልጇ አንገት ሲቆረጥ፣ ያዘለችው ልጅ ከጀርበዋ ሲወርድ የማስቆም እድል አልነበራትም። አንጀቷ እያረረ፣ ፊቷ እየጠቆረ የልጇን አንገት ሲቆረጥ ተመለከተች እንጂ።

አባት ከልጆቹ ፊት ተገድሏል፣ እናት ከፊቷ ልጇ ተሰውቷል። ይህን ግፍ ግን ያየላቸው አልነበረም። ሚስት አጋሯን ተጠነጥቃለች። ወልቃይት ጠገዴ የግፍን አይነት ቆጥሯል፣ በመከራ ውስጥ ኖሯል። በካድራ ወንዝ የወረደው መከራ የፈሰሰው የደም ጎርፍ ሳይጠራ ወልቃይት ጠገዴ ላይ ወሳኝ ነን የሚሉት በዝተዋል፣ እጃቸውን ሊያስረዝሙ የሚፈልጉት ተበራክተዋል። እውን ለዚያ በግፍ ለተቀላ ማኅበረሰብ ይህ ይገባዋልን? ቢቻል ካሳ ባይቻል ግን የጠየቀው ማንነት ያንሰዋልን? የካድራወንዝ ነዋሪዎች የደረሳበቸው የግፍ ማዕበል ሳይደርቅ፣ ከተማዋን ያደማነው የሀዘን ድባብ ሳይገፈፍ ለሌላ ሀዘን ሊዳርጋቸው የሚከጅለውን የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመቃወምና የአሸባሪው የትህነግን ግፍ ለማውገዝ አደባባይ ወጥተዋል።
ነዋሪዎቹ በሰልፋቸው አሸባሪው ትህነግ በወልቃይት ጠገዴ ያደረገው ጭፍጨፋ ይታወቅልን፣ በካድራ ወንዝ ያደረሰው የዘር ማጥፋት ወንጄል ይታወቅ፣ በማንነታችን አንደራደርም፣ ክብራችን የነካ ፍፃሜው ሞት ነው፣ ኢትዮጵያ የሰላም ሕዝብ መገኛ እንጂ የጦርነት መገኛ አይደለችም፣ የሀገራችን ሉዓላዊነት ማንም አይደፍርም፣ አሜሪካ እጇን ታንሳ የሚሉና ሌሎችን መልእክቶች አስተላልፈዋል።
ነዋሪዎቹ “በሞትን አትግፉን፣ ብትችሉ ካሳ ባትችሉ ግን ዳግም ግፍ በቃን፣ ከበደል ላይ በደል ይበቃናል፣ ከጭቆና የወጣን ሕዝብ ወደ ጭቆና መመለስ የማይታሰብ ነው” ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።

ጣልያን የካቲት 12 በአዲስ አበባ ላይ እንዳደረሰችው ግፍ ሁሉ አሸባሪው ትህነግ በማይካድራ ነዋሪዎች ላይ ፈፅሟል ነው ያሉት። ማይካድራ የጥፋት መርከብ ወደብ ናትም ብለዋል። ከአሸባሪው ትህነግ ጎን የሚሰለፍ የትኛውም ኃይል የትናንቱ የመከራ ዘመን ዳግም እንዲደገም የሚፈልግ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
መራር ዋጋ ተከፍሎ የተገኘውን ነፃነት የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኃይል ጣልቃ ገብቶ በማንነታችሁ እኔ ልወስን ሲል አንፈቅድምም ብለዋል። የወልቃይት ጠገዴ አማራዎች ያስመለስነው ማንነት እንጂ የወሰድነው መሬት የለንምም ነው ያሉት።
የአማራ ልዩ ኃይል ከወልቃይት ጠገዴ ይውጣ ማለት ከነውርም በላይ በማይካድራ ሰማእታት ላይ መሳለቅና ፈፅሞ አንቀበልም ብለዋል። “የሞትነው እኛው፣ በማንነታችን ተለይተን የተጨፈጨፍነው እኛው፣ ዙሪያ መለስ ተበዳዮች እኛው ሆነን ሳለን በውጭ ሚዲያዎች በዘመቻ የሐሰት ዜና እየተሠራብን ጩኸታችን ሊቀሙን ለሚሞክሩ መልሳችን አንድ ነው። እውነት አንዲት ናት ብትቀጥንም አትበጠስም በደላችን እስኪታወቅልን መታገላችን እንቀጥላለን” ነው ያሉት። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ከሳ እንደሚሻም ገልጸዋል።
በግፍ ቀያቸውን ለቀው የኖሩ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጆች ወደ ቃያቸው እንዲመለሱ የፌደራል መንግሥትና ሌሎች አካላት እንዲሠሩ ጠይቀዋል። ስለ ወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ማንነት ከራሱ በላይ ማንም ምስክር የለምም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ- ካድራወንዝ (ማይካድራ)
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ