
“የተዘዋዋሪ ብድር በአግባቡ አለመመለስ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንቅፋት ሆኗል”
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 04/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) ቀደም ብሎ የተሰራጨው ተዘዋዋሪ ብድር በአግባቡ ባለመመለሱ በአዲስ ለተሰራጩ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንቅፋት መሆኑን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች መምሪያ ገልጿል።
በዞኑ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ 332 ሚሊዮን 382 ሺህ ብር ለ9 ሺህ 423 ወጣቶች ብድር መሰጠቱን የመምሪያው የገበያ ልማትና ግብይት ቡድን መሪ ጳውሎስ አስማረ በተለይ ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል።
ከተሰራጨው ብድር 43 ሚሊዮን 65 ሺህ ብር በተቀመጠው ጊዜ መመለስ የነበረበት ቢኾንም ባለመመለሱ ለሌሎች ወጣቶች የብድር አገልግሎት ለመስጠት እንዳልተቻለ አቶ ጳውሎስ አብራርተዋል።
ለአብነት በ2013 በጀት ዓመት በዞኑ 74 ሚሊዮን 545 ሺህ ብር ለወጣቶች ለማበደር ቢታቀድም የተሰራጨው ብድር 3 ሚሊዮን 251 ሺህ ብር ብቻ ነው።
ብድር ማሰራጨት የቻሉትም ከአስራ አምስቱ ወረዳዎች ምሥራቅ በለሳና ማዕከላዊ አርማጭኾ ወረዳዎች ብቻ ናቸው ብሏል።
የ2009 ዓ.ም ብድር ስርጭት ላይ የነበረው የምልመላ ችግር፣ ወጣቶቹ በማኅበር ተደራጅተው ብድር ከወሰዱ በኃላ መበታተናቸው፣ ከዕቅድና ዓላማው ውጭ ገንዘቡ ማዋሉና በተቋማት በኩል የነበረው ክትትልና ድጋፍ አናሣነት የተሰራጨው ብድር በአግባቡ እንዳይመለስ ምክንያት መሆኑን ቡድን መሪው ጠቅሰዋል ።
በዞኑ ከ31 ሺህ በላይ ወጣቶች ተደራጅተው ብድር እንደሚፈልጉ የጠቀሱት አቶ ጳውሎስ መሪዎችና ተቋማት ብድሩን ለማስመለስ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል ።
በቀጣይ ብድር ሲሠራጭ ምልመላው በጥንቃቄ መታየት ያለበትና ለሚገባቸው ወጣቶች ብቻ መሰጠት እንዳለበት አመላክተዋል።
ዘጋቢ፡- አገኘሁ አበባው – ከጎንደር