
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሥራ ዕድሎች መፈጠሩን የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ንጉሡ ጥላሁን ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 04/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሥራ ዕድል ፈጠራ የ2013 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት ሀገራዊ አፈፃፀም እና የመረጃ ጥራት ዳሰሳ ውጤት የኢፌድሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ደመቀ መኮንን በሚመሩት የሥራ ዕድል ፈጠራ ብሔራዊ ምክር ቤት ቀርቧል።
የ2013 የበጀት ዓመት ሀገራዊ የሥራ ዕድል ፈጠራ ዕቅዱ ሦስት ሚሊዮን የሥራ ዕድሎች ለመፍጠር ያለመ ሲሆን በዘጠኝ ወራት ደግሞ 2 ነጥብ 55 ሚሊዮን የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ታቅዶ የተጀመረ ነው። ይህ ዕቅድ በየክልሎቹ የተከፋፈለ እና የተሰጠ ቢሆንም ክልሎች የየራሳቸውን ጸጋ ለይተው ተጨማሪ ዕቅድ ይዘዋል።
የኢፌድሪ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ንጉሡ ጥላሁን ባቀረቡት የአፈጻጸም ሪፖርት በዘጠኝ ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል፡፡
ከሥራ ዕድል ዘርፍ
• የግብርና ዘርፉ 29 በመቶ፣
• ኢንዱስትሪ ዘርፍ 30 በመቶ
• የአገልግሎት ዘርፉ 41በመቶ ድርሻ ይይዛሉ።
• ከተፈጠሩት የሥራ ዕድሎች 64 በመቶ ቋሚ ሲሆኑ 36 በመቶ ደግሞ ጊዜያዊ (ከሦስት ወራት በታች) ናቸው።
• በጾታ ስብጥር የሴቶች ድርሻ 35 በመቶ
• በገጠር የተፈጠሩት የሥራ ዕድሎች 49 በመቶ፣
• በከተማ ደግሞ 51በመቶ ድርሻ ይይዛሉ።
ኮሚሽነሩ በሪፖርታቸው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ እና የቀነሰ አፈጻጸም ያሳዩ ክልሎችን፣ በየዘርፉ ከፍተኛ መካከለኛ እና ዝቅተኛ አፈጻጸም ያሳዩ ክልሎችንና ንዑሳን ዘርፎችን በዝርዝር ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
ለሥራ ዕድል ፈጠራ በፋይናንስ አቅርቦት የተሠሩ ሥራዎችን፤ ከ2008 – 2013 ዓ.ም የተደራጁ ኢንተርፕራይዞችን የመኖር ምጣኔ ለማወቅ እና የ2013 ዓ.ም የበጀት ዓመትን የስምንት ወራት የሥራ ዕድል ፈጠራ ሪፖርት የጥራት ደረጃ ለመለካት የሚያስችለውን ጥናት ውጤት በተመለከተ ኮሚሽኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሠራቸውን ሥራዎች እንዲሁም ለዘርፉ ማነቆ የሆኑ ዋና ዋና ተግዳሮቶችን በዝርዝር አቅርበዋል።
በቀረበው ሪፖርት መነሻነትም ከምክር ቤቱ በተነሱ ሐሳቦችና ጥያቄዎች ዙሪያም ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንን የወጣቶችን የሥራ ባህልና አመለካከት መቅረጽ ሥራ ከመንግሥት ባለፈ ወላጆች ያለባቸውን ኀላፊነት እንዲሁም ወጣቶችም በአካባቢያቸው ያሉ ጸጋዎችን በመለየት ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ማኅበረሰቡ ሊወጣ የሚገባውን ሚና እና ኹሉም የሚሳተፍበት የሥራ ገበያ መፍጠር በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
የሥራ ዕድል ፈጠራን ከአረንጓዴ ልማት ጋር በማስተሳሰር በሁለት ወገን የሚጠቅም ለውጥ ማምጣት የሚቻልበትን መንገድና በተለይም ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችን ስታርታፖችን የማጠናከር ሥራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ መግለጻቸውን ከኮሚሽኑ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ