
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌደራል የጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን አፀደቀ፡፡
ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2013 ዓ.ም ( አሚኮ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ጉባኤው
የፌዴራል የጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አፅድቋል፡፡
ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳቡን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አቡ ብርኪ
ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን ለዝርዝር እይታ ወደ ቋሚ ኮሚቴው ከመራ ወዲህ በተለያዩ ጊዜያት ከአስረጂዎችና ከባለድርሻ አካላት
ጋር በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገበትና በቂ ግብዓትም የተገኘበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በውይይቱም የጥብቅና ፍቃድ አሰጣጥና አስተዳደር አገልግሎት ላይ ሰፊ የሕግ፣ የአሠራር፣ በአንዳንድ ጠበቆች ላይ የብቃትና
የሥነ-ምግባር ችግሮች እየተስተዋሉ መምጣቱን በጭብጥነት መለየታቸውን አብራርተዋል፡፡
የጥብቅና ፍቃዱ ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ቁጥጥር ስር መሆኑ አገልግሎቱ በሚጠበቅበት ደረጃ እንዳያድግና የሙያ ነጻነቱን
በጠበቀ መልኩ አገልግሎቱ እንዳይሰጥ ማድረጉን አመላክተዋል። የጥብቅና ሕጎች ሀገሪቱ ካለችበት አጠቃላይ ኢኮኖሚዊ፣
ማኅበራዊና ፓለቲካዊ እንቅስቃሴዎች አንጻር ሊኖሯት የሚያስፈልጉ የጥብቅና ድርጅቶችን በተደራጀ ሁኔታ የሚመሩ
አለመሆናቸውን በሪፖርታቸው አመላክተዋል፡፡
በረቂቅ አዋጁም አንዳንድ አንቀጾችን ሙሉ በሙሉ በሌሎች አንቀጾች ከመተካት ጀምሮ በርካታ ማሻሻያዎች መደረጋቸውንም ነው
ባቀረቡት ሪፖርት የጠቆሙት፡፡
የፌደራል የጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥና አስተዳዳር ረቂቅ አዋጅ የሀገሪቱን ዜጎች ፍትሕ የማግኘት እና የሕግ የበላይነት
በማረጋገጡ ሂደት ጠበቆችና የጥብቅና ድርጅቶች የሚኖራቸው ድርሻ የጎላ እንዲሆን እንዲሁም የጠበቆችን ብቃትና የሥነ
ምግባር ችግር የሚፈታ፣ መብትና ነጻነት የሚስጠብቅ፣ የተገልጋችን መብት የሚስከብር በመሆኑ ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን
እንዲያፀድቀው የውሳኔ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡
ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ የፌደራል የጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥና አስተዳዳር ረቂቅ አዋጅ ቁጥር
1249/2013 ዓ.ም አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
የመረጃ ምንጭ:- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማኅበራዊ ትስስር ገጽ።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m