አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በደሴ ከተማ ዘመናዊ የሚዲያ አገልግሎት መስጠት የሚችል የሕንጻ ግንባታ አስጀምሯል።

296

አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በደሴ ከተማ ዘመናዊ የሚዲያ አገልግሎት መስጠት የሚችል የሕንጻ ግንባታ አስጀምሯል።
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 03/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በራዲዮ፣ በጋዜጣ እና በቴሌቪዥን እንዲሁም በአዲሱ
የሚዲያ አውታር ጭምር የሀገር ውስጥና የውጭም ፣ በከተማና ገጠር የሚኖረውን ሕዝብ ለማገለገልና ዘመኑን የዋጀ ሚዲያ
ለመሆን እየተጋ ይገኛል፡፡
የኮርፖሬሽኑን ተደራሽነት ይበልጥ ለማሳደግ ልዩ ልዩ የማሻሻያ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ፤ የዚሁ አንዱ አካል የሆነው ዘመናዊ
የሚዲያ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የሚዲያ ሕንጻ ግንባታ ዛሬ በደሴ ከተማ ተጀምሯል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ እንዳሉት ሕንጻው ሁለት የቴሌቪዥን ስቱዲዮ እንደሚኖረው እና የሬዲዮ
ማሰራጫዎችንም ይዟል፡፡ ተቋሙ ለወሎ ሕዝብ የመገናኛ ብዙኃን ማእከል በመኾን ያገልግላል ነው ያሉት፡፡
አሚኮ አሁን ላይ በ6 ቋንቋዎች ሥርጭት እያስተላለፈ እንደሚገኝ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በቅርቡ የሰው ኀይል
በማሟላት በአረበኛ ቋንቋ ሥርጭት ለመጀመር እየተሠራ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የአማራ እና የትግራይ ሕዝቦችን
ሕዝባዊ መስተጋብር ለማጠናከር እየሠራ እንደኾነም አመላክተዋል፡፡
አሚኮ “አማራ ኅብር” የተሰኘ 2ኛ የቴሌቪዥን ጣቢያ ለማስጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁን ጠቁመዋል፡፡ ይህ ጣቢያ በአማራ ላይ
የተነዛውን የሐሰት ትርክት ለማስተካከል እንዲቻል ከአማርኛ ውጭ ባሉ ቋንቋዎች የተለያዩ ፕሮግራሞች እየሠራ እንደሚያሰራጭ
ነው የገለጹት፡፡
ጣቢያው ከአማራ አጎራባች ከኾኑ ክልሎች ጋር ይበልጥ ትስስር ለመፍጠር በሱማሌኛ፣ በአፋርኛ እና በጉምዘኛ ቋንቋዎች
የሚሰራጩ ፕሮግራሞች እንደሚኖረውም ተጠቅሷል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከኹሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ወኪል እንዲኖረው ለማድረግ እየተሠራ እንደኾነና በዚህ ዓመት መጨረሻ በኹሉም
ከልሎች አሚኮ ወኪል እንደሚኖረው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል፡፡
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የአማራ ሕዝብ ሀብት ቢኾንም ለሌሎችም እንደ ድልድይ ኾኖ ማገልገል ስላለበት ለቦርድ ቀርቦ ከጸደቀ
በውጭ ሀገር ወኪል እንዲኖር እያደገም ሲሄድ ማሰራጫ እንዲኖረው ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ አስገንዝበዋል፡፡ ለዚህም
ሥራ የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቦርዱም ክትትል እያደረገ የአሚኮ
ቤተሰብም ለሚዲያው ውጤታማነት በጋራ እየሠራ ተመራጭ ጣቢያ እንደሚኾን ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ምስጋናው ብርሃኔ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“የኬንያው ፕሬዝዳንት ቆይታ ውጤታማ ነበር” አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
Next articleየኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌደራል የጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን አፀደቀ፡፡