በክልሉ አንድ ወር በማይበልጥ ጊዜ ዘመቻ ከ207 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች የፀና የሦስተኛ ወገን መድን ዋስትና እንዲኖራቸው ማድረጉን መድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

345

ባሕር ዳር፡ መስከረም 8/2012 ዓ.ም (አብመድ) ዋጅ ቁጥር 799/2005 ከወጣ ጀምሮ ሁሉም ተሽከርካሪዎች የፀና የሦስተኛ ወገን መድን ዋስትና ሳይኖራቸው ማሽከርከር እንዳይችሉ ያግዳል፤ በቅርቡ መድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ባደረገው ፍተሻ ግን በአማራ ክልል 50 ከመቶ የሚሆኑት ተሽከርካሪዎች ያለመድን ዋስትና እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ማረጋገጡን ነው የገለጸው፡፡ እንደ መድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ማብራሪያ ከሆነ ጉዳዩ አዋጁን ያለመገንዘብ ሊሆን ይችላል በሚል ወደ ቅጣትና እርምጃ አልተገባም፡፡

የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ባሕር ዳር ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ አዝመራው በቀለ እንደተናሩት ጉዳዩን ሥርዓት ለማስያዝ ከሐምሌ 10 እስከ ነሐሴ 30 /2011 ዓ.ም በተካሄደው የንቅናቄ ሥራ በሀገሪቱ ከ207 ሺህ በላይ መኪኖች የፀና የሦስተኛ ወገን መድን ዋስትና እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡

ከመስከረም 1 እስከ 30/2012 ዓ.ም ደግሞ ሕግ የማስከበር ሥራ ተጀምሯል፡፡ የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ባሕር ዳር ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ አዝመራው በቀለ “ከዚህ በኋላ ተሽከርካሪዎች የፀና የሦስተኛ ወገን መድን ዋስትና ሳይኖራቸው ጎዳና ላይ መታየት አይችሉም” ብለዋል፡፡ ሥራ አስኪያጁ መንጃ ፈቃድ ለመስጠትም ዋስትናው እንደ አንድ መስፈርት እንደሚጠየቅ ተናግረው መንገድ ትራንስፖርት እና ፖሊስ የቁጥጥሩን ክንውን በመደበኛ ሥራነት ይዘው እንዲሠሩም መግባባት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ

Previous articleበቀዳማዊት እመቤቷ እየተገነቡ ከሚገኙት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለማስተማር ዝግጁ የተደረጉ መኖራቸው ተገለፀ፡፡
Next articleየአማራ ክልል የመንግሥት ግዥ እና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዓለማቀፍ ግዥዎችን ለመፈፀም መቸገሩን አስታወቀ፡፡