የአማራ ክልል የመንግሥት ግዥ እና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዓለማቀፍ ግዥዎችን ለመፈፀም መቸገሩን አስታወቀ፡፡

1239

ባሕር ዳር፡ መስከረም 8/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ልየዉ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እንደተናገሩት በ11 ከተሞች እና የግንባታ ተቋማት ለአማራ ክልል የመሠረት ልማት ማስፋፊያ የሚዉሉ ዶዘር፣ ሮለር፣ ሎቤድ፣ ኤክስካባተር እና ሌሎች የግንባታ ማሽነሪዎችን እንዲሁም ለአማራ ክልል የቴክኒክ ሙያ ኮሌጆች ማሰልጠኛ የሚዉሉ መሳሪያዎችን ለመግዛት ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ አሸናፊው ከተለየ ቆይቷል፡፡

የግዥ ተቋሙ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 400 ሚሊዮን ብር ገቢ በማድረግ ለጨረታ አሸናፊዎች የሚከፈል የውጭ ምንዛሬ ቢጠይቅም ማግኘት አልተቻለም፡፡ የግንባታ ማሽነሪዎች እና ማሰልጠኛ መሳሪያዎችን ለመግዛት አንድ ሚሊዮን 771 ሺህ 500 ገዳማ ዩሮ እና 9 ሚሊዮን 49 ሺህ የሚጠጋ የአሜሪካ ዶላር አስፈልጎት ጥያቄውን ከ22 ወራት በፊት ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቢያቀርብም የውጭ ምንዛሬው ስላልተፈቀደለት መቸገሩን አስታውቋል፡፡

ለመንገድ ግንባታ አገልግሎት የሚውል 16 ማሽነሪዎች በ69 ሚሊዮን ብር ተገዝተው እንዲቀርቡለት የክልሉን ግዥ እና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ቢጠይቅም መሳሪያዎች ተገዝተው ስላልቀረቡለት መቸገሩን ደግሞ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አስታውቋል፡፡ የማሽነሪዎቹ አለመቅረብ መሠረተ ልማትን በከተማ አስተዳደሩ ማስፋፋት እንዳላስቻለም ነው የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ መላክ አድማሱ ያመለከቱት፡፡

የአማራ ክልል የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የግንባታ መሳሪያዎች እና ሌሎች መሳሪያዎችን ለመግዛት ከ22 ወራት በላይ የውጭ ምንዛሬ በመጠበቅ ላይ በመሆኑ ተፈላጊ ማሽነሪዎች ተገዝተው ባለመቅረባቸው በክልሉ ልማት ላይ ተጽእኖ እያሳደረ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ኤጄንሲው በውጭ ምንዛሪ ማጣት ምክንያት አገልግሎት የሚሰጣቸውን ተቋማት ማርካት እንዳልቻለና ተቋማቱ ግዥ ሳይፈጸም በጀት ዓመቱ ሲያልቅባቸው ሐሳባቸውን እየቀየሩ ጭምር መቸገሩንም አመልክቷል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምላሽ እንዲሰጥ አብመድ ለሦስት ወራት በተደጋጋሚ ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም፡፡

ዘጋቢ፡- ተመስገን ዳረጎት

Previous articleበክልሉ አንድ ወር በማይበልጥ ጊዜ ዘመቻ ከ207 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች የፀና የሦስተኛ ወገን መድን ዋስትና እንዲኖራቸው ማድረጉን መድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
Next articleየአማራ ምሁራን መማክርት ጉባዔ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት