
“ከገንዘብ ላይ ገንዘብ ቢደራረብ ንብረት
ከሁሉም በላይ ነው ለሐበሻ ነፃነት”
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 03/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) እግሬ መልካም ቦታ አደረሰኝ፣ ዓይኔ መልካም ነገር አሳዬኝ፣ ጆሮዬ መልካም ነገር አሰማኝ፣ አዕምሮዬ ክፉውን አስረስቶ መልካም ነገር አስታወሰኝ። አዳራሹ በእልልታ ተጀምሮ፣ በልልታ ተፈጸመ። ይህ ለዚያ አዳራሽ የመጀመሪያው ነው። አፍ ኖሮት ቢናገር፣ አንደበት አውጥቶ ቢመሰክር ይህንስ አይቼውም አላውቅ ይል ነበር። ከዚያ በፊት በእርሱ ጥላ ሥር የሚሰበከው ስበከት፣ የሚዘመረው ሥርዓት የተለዬ ነበርና።
ነፃነት ከሀብት፣ ከንብረት ከሁሉም በላይ ነው። ሀብትና ንብረት ያለ ነፃነት ምንም ናቸው። ነፃነት ያለው ድህነት ጌጥ ነው። ነፃነት ኩራት፣ ነፃነት አይሸነፌነት፣ ነፃነት ፅናት፣ ነፃነት በረከት ነውና። ነፃነታቸውን ከአሸባሪው ሕወሓት እጅ ላይ ያስመለሱት የሑመራ ነዋሪዎች በአንድ አዳራሽ ተሰባስበዋል። ከአዳራሹ ዘግይተው የገቡት ቀድመው የገቡትን ሰርግ እንዳሰረጉ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ ይሏቸዋል። ቀድመው የገቡት ደግሞ ከመቀመጫቸው እየተነሱ እንኳን አብሮ ደስ አለን፣ እንኳን ይህችን ቀን ለማዬትና ያ ዘመን አልፎ ለመገናኘት አበቃን ይባባላሉ፡፡
ነዋሪዎቹ “ጉደኛ” በሚሉት አዳራሽ ውስጥ ጥግ ይዤ ተቀምጫለሁ፣ ወጭና ገቢውን እታዘባለሁ። እንቅስቃሴዎች ሁሉ እየገረሙኝ ነው። የአዳራሹ ወበቅ ትንፋሽ ሊያሳጥረኝ ምንም አልቀረውም። በብጣሽ ወረቀት ፊቴን እያሽረፈረፍኩና አየር እየሳብኩ እንቅስቃሴዎችን መቃኘት ላይ ነኝ።
ውይይቱ ሊጀመር ነው። መድረክ መሪው የድምፅ ማጉያውን ይዞ “ውድ እንግዶች እንደምን ዋላችሁ፣ እንኳን ለዚህ ቀን አበቃን” ሲል ከዚህ ቀደም እንደማውቀው ጭብጨባ ብቻ አልነበረም፣ እልልታ ቀለጠ። ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ እልልታ። ራሴን ጠየኩ። ብቻ ያልገባኝ ሚስጥር አለ። በዚህ አዳራሽ ውስጥ በአማርኛ አውርታችሁ ታውቃላችሁ? አለ መድረክ መሪው። ቀዝቅዞ የነበረው እልልታ ድጋሜ ደመቀ። ጭብጨባው አስተጋባ። አሁን ሚስጥሩ ተገልጧል። በአማርኛ ለመወያየት በመቀመጣቸው ነበር ያ ሁሉ እልልታና ጭብጨባ።
ወይ ነፃነት ይህን ያክል ኃያል ኖሯል። በሀገሩ ላይ ነፃነቱን ተገፍፎ በስቃይ የኖረውን ሕዝብ ነፃነቱን ሲያገኝ የሚያሳዬውን ደስታ ነፃ ሆኖ ለቆዬ ሠው ቢነግሩት ላይረዳ ይችላል። የነፃነትን ዋጋ የሚያውቀው፣ የነፃነትን ስሜት የሚረዳው ነፃነትን አጥቶ የቆዬ ብቻ ነው። በውጭ ጠላት ነፃነቱን ያልተደፈረው ኩሩ ሕዝብ፣ ሞቶ ባኖራቸው፣ መርቶ ቤተ መንግሥት ባስገባቸው፣ ከጫካ አውጥቶ ዙፋን ላይ ባስቀመጣቸው የሀገሩ ልጆች ነፃነቱን ተቀማ። የደም ካሳው ፍቅርና ክብር ሳለ መከራና ስቃይ ሆነ። ተጎትቶ ዙፋን የያዘው፣ ሀገር የገዛው ቡድን ኩሩዎችን ገፋቸው፣ አዳፋቸው፣ አሰቃያቸው፣ ክብራቸውን ገፈፈው። ጎትተው ያወጡትን ገፍተው አወረዱት፣ ሞተው ያከበሩትን ሞተው አዋረዱት። የእውነት ቀን መጣ፣ የፍትሕ ፀሐይ ወጣ።
ውይይቱ ተጀምሯል። የሑመራ ነዋሪዎች በወቅታዊ ሀገራዊና አካባቢያዊ ጉዳይ ከአስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ለመምከር ነበር በአዳራሹ ውስጥ የተሰባሰቡት።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን የብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አማረ ጎሹ ስለ ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ፣ ስለ ቀጣናዊ የፖለቲካ አሰላለፍና የውጪው ዓለም በኢትዮጵያ ላይ ስላለው ወቅታዊ ምልከታ በአዳራሹ ውስጥ ላሉ ሰዎች ገለፃ አደረጉ። ኢትዮጵያ ልታካሂደው ቀነ ቀጠሮ የቆረጠችለትን ምርጫ ያልተሳካ ለማድረግ፣ የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት እንዳይደረግ ማደናቀፍ፣ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መልካም ወዳጅነት እንዲሻክር፣ የሕወሓት አሸባሪ ቡድን ዳግም እንዲያንሰራራ የውስጥና የውጭ ኃይሎች አጥብቀው እየሠሩ መሆናቸውን ገለፃ አደረጉ። ለኢትዮጵያ ዘመናትን በዘለቀው ታሪኳ ፈተና አዲስ እንዳልሆነና ፈተናዎችን ሁሉ እያሸነፈች ማለፏንም አስረዱ።
በአካባቢው የአሸባሪው የሕወሓት ተላላኪዎችና ደጋፊዎች ለእኩይ ዓላማቸው ሊንቀሳቀሱ እንደሚችሉም አሳሰቡ። የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመድፈር አማራን ማዳከምና ኢትዮጵያውያንን በየ አቅጣጫው ማተራመስ የጠላቶች የዘወትር ሥራ ስለመሆኑም ገለፁ።
ተወያዮቹ በጥሞና እያዳመጡ ነው። ስለ ወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ ወሳኙ ሕዝብ እንጂ ማንም አይደለም። ጭብጨባው አወካ። ይህን እውነታ የሚቀይር አንዳች ኃይል የለም፣ ወልቃይት ጠገዴ አማራ ነው፣ የተገኘውን ድል በትህትና እና በሆደ ሰፊነት ማዝለቅ፣ በጥልቅ ሕዝባዊ ኃላፊነት መጠቀም፣ አብሮነትን ማጠናከር፣ ለዳግም ባርነት አለመዘጋጀት ያስፈልጋል ሲሉ ጭብጨባው ቀለጠ እልልታው ደመቀ። እልልል….. ደስታ የተመላበት የመልካም እናቶች ድምፅ።
የተፈናቀሉ ወገኖችን ማቋቋምና አብሮ መሥራት፣ ግፍ ያደረሱ አካላት በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ በጋራ መሥራት፣ የፀጥታ ኃይሉን ማጠናከር ጎን ለጎን የልማት አቅምን ማጎልበት ለወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ወሳኙ ጉዳይ ነው አሉ። ጥግ ላይ እንደተቀመጥኩ ሐሳቦችን ማስታወሻዬ ላይ እያሰፈርኩ ሁኔታውን መቃኘቱን ቀጥያለሁ።
ነዋሪዎቹ ሀሳብ መስጠት ጀመሩ። ነፃነታችንን ወደባርነት ሊመልሱን የሚታገሉ የውስጥም የውጭም ጠላቶች አሉብን፣ ነገር ግን የመከራን ዘመን ተሻግረነዋል፣ ይህንም እንሻገረዋለን። የፈራረሰው የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን እሳቤውም እንዲፈራርስ በጋራ መሥራት ይገባናል አሉ። በውስጥ ያሉ ባንዳዎችን ማፅዳት ይገባል፤ የአማራ ሕዝብ ከትግሉም አይመለስም፣ ማንነቱን አሳልፎ አይሰጥም፣ ብዙ ፈተናዎችን አልፎ የመጣ በመሆኑ ይህንንም ያልፈዋል፣ አባቶቻችን የሰጡንን ነፃ ሀገር ለማንም አሳልፈን አንሰጥም የነዋሪዎች ሐሳብ ነው።
አብሮነትን ማሳደግ ይገባል፣ የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ በዋዛ የሚታይ አይደለም አሉ ነዋሪዎቹ። የወልቃይት እናቶች የግፍ እሳት አርግዘው እንደኖሩና በቅርብ ግን እሳቱን ተገላግለው ነፃ መሆናቸውን በደስታ ገለፁ። የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ስለ ፍቅርና ስለ ሀገር ክብር ሲሉ መሞታቸውን አነሱ። ነዋሪዎቹ የመብራትና የውኃ ጥያቄዎች እንዲፈቱም ጠየቁ።
ሥርዓታቸው፣ ትህትናቸው፣ ፍቅራቸውና መከባበራቸው የሚገርም ነበር። ሕወሓት ሲያደርስባቸው የነበረው ግፍ በአዳራሹ ውስጥ ሲተርኩት ያሳዝናል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን የብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አማረ ጎሹ ለቀረበላቸው ጥያቄና አስተያየት መልስ መስጠት ጀመሩ። ለሕዝብ የተመቹ ያልሆኑና የሕዝብን ጥቅም አሳልፈው የሚሰጡ የሥራ ኃላፊዎችን መርህን መሰረት አድርገው እርምጃ እንደሚወስዱ ገለፁ። ከጠላት ጋር የሚላላኩትን ሕግን በማስከበር እንፈታለን አሉ። ወልቃይት ጠገዴ አማራ መሆኑ ታውቆ ያደረ ነው፣ ነጣጣይ አጀንዳዎችን መቀበል ተገቢ አይደለም፣ አማራን ለማዳከምና ለመከፋፈል የሚተጉትን ጆሮ እንዳይሰጧቸው አሳሰቡ። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ከአማራነት የማይነጠል ነው፣ ሰውም ቆፍጣና ነው ድንበሩም ተከዜ ነው። ጭብጨባው አገረሸበት።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አስተዳደር አሸተ ደምለው ኢትዮጵያዊነት ዓለትነት ነው፣ ብዙ መዶሻዎች ዓለቱን ለመፈርከስ ሊነሱ ይችላሉ፣ ነገር ግን በመዶሻቸው ተፈርክሰው ይጠፋሉ እንጂ ኢትዮጵያን ማጥፋት አይቻልም አሉ። ኢትዮጵያ አልማዝ ናት፣ ለማፍረስ የሚመኟት፣ ማፍረስ የማይችሏት ውድና ውብ ሀገር መሆኗን አነሱ። ኢትዮጵያ ጠላቶቿ የበዙባት የነፃነት ተምሳሌት ስለሆነች ስለሚፈሯት ነው፣
ይወድቃሉ ሲሉን የምንነሳ፣ ያልቃሉ ሲሉን የምንበዛ ነን፣ በሐሳብና በተግባር አንድ ስንሆን ጠላት ቀዳዳ ያጣል አሉ። የመብራት እና የውኃን ችግር ለመቅረፍ የሚቻለው ሁሉ እየተደረገ መሆኑን ገለጹ፣ ትዕግስት እንደሚጠይቅና ችግሩም እንዲቀረፍ የተለያዩ አማራጮችን እየተጠቀሙ መሆናቸውን ተናገሩ።
ቀደም ባለው ጊዜ በዚያ አዳራሽ ውስጥ መከፋፈል ተሰብኮበታል፣ የአንድነት ውይይት ናፍቆታል፣ የፍቅር ለዛ ጠፍቶበት ኖሯል። አንድነት ወዳድ ሕዝብ በሰው ፊት ተሸማቆበታል። አሁን ሌላ ዘመን መጥቷል። በዚያ አደራሽ ደስታ ታይቶበታል። ፍቅር ተሰብኮበታል። ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብሎበታል። አንድነት ተዘምሮበታል። አብሮነት ጎልብቶበታል። እንኳን ሰዎቹ አዳራሹ ሳይገርመው አልቀረም።
ውይይቱ አብቅቷል። በእልልታ ተጀምሮ በእልልታ ተፈፅሟል። ነዋሪዎቹ ከአዳራሹ መውጣት ጀምረዋል፣ በዚህ መካከል የመድረኩን ቴክኒክ ሲቆጣጠር የነበረው ወጣት ጎንደርኛ ሙዚቃ ከፍ አድርጎ አሰማ። ሲወጡ የነበሩ ነዋሪዎች መውጣቱን ትተው ወደ ውዝዋዜ ገቡ። እናቶችና አባቶች በአንድነት ጨፈሩ፣ በአንድነት ዘመሩ። እልልታው ደራ ጭፈራው ደመቀ።
“ድል ያለ ድል ነው ወገን ተሰብሰብ
ዳግም ሆነናል አንድ ቤተሰብ
ክብሩ ሲመለስ ማንነቱ የሰው
ትንሽ ትልቁን ደስታ አስለቀሰው
የወገኔ ክብር የኢትዮጵያ ከፍታ
አይነቃነቅም ከአሁን ወዲያ ለአፍታ” የከያኙ ግጥሞች እየተከታተሉ ይንቆረቆራሉ። በዘፈኑ የታጀቡት ነዋሪዎች በእልልታ ይዘላሉ። አጄብ ነው። የደስታ እንባ፣ ልብ የሚነካ ስሜት። ግሩም ነበር። በሐሳብ ባሕር ውስጥ የሚያሰምጥ፣ አሁን ላይ ሆነው ትናንትን የሚያሳይ፣ የዛሬ ደስታ በስንት መከራ የመጣ መሆኑን የሚያስታውስ፣ ነፃነት በገንዘብ የሚረሳ ቢሆን ኖሮ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ጉዳይ ተዳፍኖ በቀረ ነበር።
“ከገንዘብ ላይ ገንዘብ ቢደራረብ ንብረት
ከሁሉም በላይ ነው ለሀበሻ ነፃነት” ሀብትና ንብረት ከነፃነት እጅግ ያነሱ ነበሩና ነፃነትን ለማስረሳት የተዘረጉ ገንዘብ የያዙ የሕወሓት እጆች መና ቀርተዋል። ፊት ተነስተዋል፣ ተቀባይነት አጥተዋል። ማንነትን ለመርሳት ገንዘብ ከመቀበል ይልቅ ስለ ማንነት ሞትን ለመቀበል ተዘጋጁ። ለኢትዮጵያውያን ከነፃነት ጋር የሚወዳደርባቸው ነገር የለም። ሀብት አላፊ ጠፊ ነው፣ ነፃነት እና ያልተበረዘ ማንነት ግን ኩራት፣ ታሪክ ነው፣ ለዚያም ነው ሞተው ያስመለሱት።
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ