የጤና ሚኒስቴር የድንገተኛ፣ አደጋና ጽኑ ህክምና የአምስት ዓመት መሪ ዕቅድ ይፋ አደረገ።

240

የጤና ሚኒስቴር የድንገተኛ፣ አደጋና ጽኑ ህክምና የአምስት ዓመት መሪ ዕቅድ ይፋ አደረገ።
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 02/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የድንገተኛ አደጋና ፅኑ ህክምና የአምስት ዓመት መሪ ዕቅድ፣ የጤና ሚኒስቴር
በመተግበር ላይ ባለው ሁለተኛው የአምስት ዓመት የጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ለተካተቱት የጤናው ምላሽ
ስርዓት ማሻሻል፣ ከድንገተኛ የጤና አደጋዎች ኅብረተሰቡን መከላከል፣ በቤተሰብ ጤና አስተዋጽኦ ማድረግ እንዲሁም የጤና
ሽፋንን ለሁሉም የማዳረስ ሥራዎችን ለማስፈጸም ሀገራዊ አቅጣጫን የሚያስቀምጥ ነው።
ይህ ሀገራዊ የአምስት ዓመት የጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከሀገሪቱ የአስር ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ጋር የተናበበ
ሲሆን በዋናነት ለጤናው ዘርፍ የተለዩ ግቦችን በማስቀመጥ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
መሪ ዕቅዱ 10 ስትራቴጂካዊ ግቦች ያሉት ሲሆን ማሕበረሰብ በዘርፉ ውስጥ ያለውን ተሳትፎ የሚያሳድግበትን መንገድ፣
የድንገተኛ፣ የአደጋና ጽኑ ህክምና አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞችና የአገልግሎት ሰጪ ማዕከላት አቅም የሚገነባበትን አግባብ
እንዲሁም የመድኃኒትና የህክምና ቀሳቁስ አቅርቦት የሚሻሻልበትን አሠራር ለመዘርጋት አቅጣጫ የሚጠቁም እንደሆነም
ተመላክቷል።
በዕቅዱ ላይ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና ከክልል ጤና ቢሮ ባለሙያዎች፣ ከሌሎች አጋር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና
የመንግሥት ተቋማት፣ በተለያዩ ደረጃዎች ከሚገኙ የሙያ ማኅበራት፣ የግሉ ዘርፍ አካላት እና አጋር ድርጅቶች ጋር ውይይት
እንደተደረገም ጤና ሚኒስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።
በዕቅዱ ማብሰሪያ መርሃግብር ላይ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ሀገራችን ባለፉት ዓመታት የጤና ዘርፉን ለማሻሻል
እየተጋች ሲሆን የድንገተኛ፣ የአደጋና የጽኑ ሕክምና ሥራዎች ላይም የተሻለ ለውጥ ለማምጣት የመሪ ዕቅዱ መዘጋጀት የተቀናጀ
ትግበራ ለማካሄድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ይህ አገልግሎት ከማኅበረሰብ ጀምሮ የቅድመ ጤና ተቋም የተቀናጀ የማኅበረሰብ ጤና እና የአንቡላንስ ስምሪት ሥርአትን
መገንባት፣ በጤና ተቋማት ቀልጣፋና ጥራቱን የጠበቀ ህይወት አድን ህክምና መስጠት፣ የህሙማንን ቅብብሎሽ በማሳለጥ
አላስፈላጊ መዘግየቶችን መቀነስ፣ ለማንኛውም የጤና እክሎች መልስ መስጠት የሚያስችል አቅምን በየደረጃው መፍጠርና
መረጃን ለውሳኔ በመጠቀም ላይ የሚያጠነጥን፣ የላቀ ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ያስችላል ነው የተባለው፡፡
ይህንን የአምስት ዓመት መሪ ዕቅድ በአግባቡ ተግብሮ ለኅብረተሰቡ በሁሉም ደረጃ የተቀናጀ፤ የተናበበ፤ ወቅቱን እና ጥራቱን
የጠበቀ የድንገተኛና ጽኑ ህክምና አገልግሎት ለማቅረብና አግባብነት ያለው የጤና ሥርዓትን በመዘርጋት በድንገተኛ አደጋ እና
ጽኑ ህመም የሚከሰቱ ህመሞችን፣ የአካል መጉደልን እና ሞቶችን በመቀነስ ጤነኛና አምራች ዜጋን ለመፍጠር በሚደረገው
ርብርብ ሁሉም የራሱን አስተዋጽዖ እንዲያበረክትም ሚኒስትሯ አሳስበዋል።
የአምስት ዓመታት መሪ ዕቅዱን ለመተግበር የ200 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በጀት የሚያስፈልግ ሲሆን ይህም ከመንግሥት
በሚመደብ በጀትና ከለጋሽ አካላት በሚደረግ እገዛ የሚሟላ እንደሚሆን ተመላክቷል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበመጀመሪያ ምእራፍ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ‘የዓለም አቀፍ ጥምረት ለኢትዮጵያ ‘ኩባንያ ሥራ አስፈጻሚዎች ተናገሩ።
Next articleበትግራይ ክልል የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሠራ እንደሚገኝ ጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡