ከሁለት ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሳተፋቸውን የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡

175
ከሁለት ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሳተፋቸውን የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 02/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከቀለም እና ሙያ ትምሕርት በላይ መሬት ላይ ያለን እውነት ይገልጣል፤ ሰውነትን በሥራ፣ በጎነትን በተግባር ያለማምዳል ተብሎም ይታሰባል፡፡ ለታዳጊዎች የሀገር ፍቅር ዕሳቤን፣ የበጎነት ሃሴትን እና የርስ በዕርስ ትውውቅንም ከፍ ያደርጋል፤ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት፡፡ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ደስ እያላቸው ሲሳተፉ ከትርክት የተሻገረ እውነትን እና ከጽንሰ ሃሳብ ያለፈ ክህሎትን ወገኖቻቸውን እየደገፉ ሀገራቸውን እየታደጉ የቀጣይ ራዕያቸውን ይማሩበታል፡፡
የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተለመደ የመጣ እና ባለቤት ያገኘ በጎ ተግባር ነው፡፡ የወጣቶቹን የቀጣይ ሀገር የመረከብ ኀላፊነት ትከሻቸውን ቀስ በቀስ ሸክም እያለማመደው መሆኑን የሚያምኑም በርካቶች ናቸው፡፡
የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የክረምት እና በጋ በሚል ለኹለት ተከፍሎ እንደሚሠራ በአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የወጣቶች ማካተት ንቅናቄ ዳይሬክተር አቶ አወቀ መነግሥቴ ገልጸዋል፡፡ ያለፈውን ዓመት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መስከረም ላይ ለተሳታፊ ወጣቶች እውቅና በመስጠት ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
ቢሮው በበጋው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 3 ሚሊዮን 162 ሺህ 636 ወጣቶችን በተለያዩ መስኮች ለማሳተፍ ማቀዱንም ገልጾ ነበር፡፡ የወቅቱ የዓለማችን ግንባር ቀደም የጤና ስጋት የሆነው የኮሮናቫይረስ በሀገሪቱ መከሰቱን ተከትሎ በርካታ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎች ተጎድተው እንደነበር አቶ አወቀ አስታውሰዋል፡፡ ይህም የበጋውን የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከምንጊዜውም በላይ ተጠባቂ እና ትርጉም ያለው አድርጎት ነበር ነው ያሉት፡፡
ከ17 በላይ ተቋማትም ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ መዋቅር በመዘርጋት በበጋው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶቹ የሚሠሯቸውን ተግባራት ለይቶ በማቀድ እንደተጀመረ ነግረውናል፡፡ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ግንዛቤ ፈጠራ፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብ፣ ማኅበራዊ አገልግሎት፣ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ ድጋፍ ለሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ማድረግ፣ በሕግ ማስከበር እንቅስቃሴው የተሳተፉ አካላትን በደገፍ፣ የሚሊሻ አባላትን ሰብል መሰብሰብ፣ አንበጣ መከላከል፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የሚጎዳውን ሰብል መሸከፍ፣ ተፈናቃዮችን መደገፍ፣ ደም ልገሳ እና የመራጮች ምዝገባ ግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች በበጋው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶቹ የተሳተፉባቸው ተግባራት ነበሩ ተብሏል፡፡
በበጋው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 2 ሚሊዮን 122 ሺህ 869 አካባቢ ወጣቶች ተሳታፊ ነበሩ ያሉት አቶ አወቀ ይህም የእቅዱን 67 በመቶ የሸፈነ ነበር ብለዋል፡፡ ወጣቶቹ በአበረከቱት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መንግሥት እና ሕዝብ ያወጡት የነበረውን ከ 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ በቅርቡም የበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይፋዊ መዝጊያ ተደርጎ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ትውውቅ እንደሚደረግ አቶ አወቀ ለአሚኮ በሰጡት የስልክ ማብራሪያ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ለውጭ ኃይሎች ልናረጋግጥላቸው የምንወደው የወልቃይት ጠገዴ አማራዎች ያስመለስነው ማንነት እንጂ የነጠቅነው መሬት የለም” አቶ አሸተ ደምለው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አስተዳዳሪ
Next articleበመጀመሪያ ምእራፍ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ‘የዓለም አቀፍ ጥምረት ለኢትዮጵያ ‘ኩባንያ ሥራ አስፈጻሚዎች ተናገሩ።