
“ለውጭ ኃይሎች ልናረጋግጥላቸው የምንወደው የወልቃይት ጠገዴ አማራዎች ያስመለስነው ማንነት እንጂ የነጠቅነው መሬት የለም” አቶ አሸተ ደምለው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አስተዳዳሪ
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 02/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አስተዳደር የሑመራ ከተማ ነዋሪዎች የአሸባሪው ትህነግ ግፍና የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል። ሰላማዊ ሰልፉን ያካሄዱት የከተማዋ ሴቶች ናቸው።
የከተማ ነዋሪዎች በሰላማዊ ሰልፋቸው በውጭ ሀገራት የሚደረገውን ጣልቃ ገብነት አውግዘዋል። ስለ ማንነታቸው ከእነርሱ በላይ ማንም ሊናገር እንደማይችልም ገልጸዋል። በሰልፉ ላይ የተሳተፉት መምህርት አርሴማ ሰረበ በአሸባሪው ትህነግ ለብዙ ጊዜ ተጨቁነናል፣ ትህነግ በአማራ ላይ ግፍና በደል ፈፅሟል፣ ለዓለም አቀፉ ማኅረሰብ ድምጻችን ለማሰማት ነው የወጣነው ብለዋል።
በውስጥ ጉዳያችን ማንም ጣልቃ እንዲገባ አንፈቅድም፣ ለዓመታት ተጨቁን ስንኖር የፈታልን አልነበረም፣ ወንድም፣ እህትና ወገን ቀብረን ነው ነፃነት ያየነው፣ መንግሥታት ከወንጀለኛ ጋር ሳይሆን ከንጹሃን ጎን ሊቆሙ ይገባል ነው ያሉት።
ወይዘሮ ስመኛት ገናናው እንዳሉት ለ30 ዓመታት ግፍ ደርሶብናል፣ ተጨቁነን ስንኖር ማንም የሰማን አልነበረም፣ ዛሬ ላይ ነፃነታችንን ሊሰሙን ይገባል፣ ትናንት፣ ዛሬና ነገም አማራ ነን ይህ ሊከበር ይገባል ብለዋል።
ወይዘሮ ጥበበ መኮንን “ማንነታችን አስከብረን እንኖር ዘንድ ለማሳወቅ ሀሳባችን ይዘን ወጥተናል” ብለዋል። ነፃነታችንን አስከብረን፣ ማንነታችን አማራ ድንበራችን ተከዜ መሆኑን የዓለም ሕዝብ ሊያውቅልን ይገባል ነው ያሉት።
ማይካድራ ላይ የተፈፀመውን ግፍ ያላየችው አሜሪካ ነፃ ስንሆን አለሁ ማለቷ ተቀባይነት የለውም፣ የአሜሪካ አሻጥር ኢትዮጵያን በእጅ አዙር ለመግዛት መሆኑንም ተናግረዋል።
በሰልፉ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የሑመራ ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በሪሁን ኢያሱ በሑመራ ከተማ ሀሳብን በሰላማዊ ሰልፍ መግለጽ ይቅርና አንድ ለአንድ እንኳን ተገናኝቶ መወያየት የማይቻልበት ጊዜ እንደነበር ነው ያስታወሱት።
ሴቶች ሀብትና ንብረት እንዳያፈሩ ተደርገው ሲጨቆኑ መቆዬታቸውንም አስታውሰዋል። የወልቃይት ጠገዴ አማራዎች የኢትዮጵያን አንድነት የሚፈልጉ መሆኑንም አስታውቀዋል። የትናንቱ ጭቆና ሳይሽር ሌላ በደል እንዲደርስ የሚሹትን አንቀባለቸውም ብለዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አስተዳዳሪ አሸተ ደምለው በማንነታችን እንደማንደራደር ሊታወቅልን ይገባል ብለዋል። የወልቃይት ሕዝብ ከመዋቅራዊ ጭቆና አልፎ የተጠና የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጸምበት መቆየቱንም ገልጸዋል። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ “ከከፋኝ እስከ ሰላማዊ ትግል” ድረስ ለዓመታት መታገሉንም አስታውሰዋል። አሸባሪው ትህነግ ሀገር ከከዳበት ጊዜ ጀምሮ በተጀመረው የህልውና ሕግ የማስከበር ዘመቻ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ጋር በመሆን ትግል መደረጉን ነው ያስታወሱት።
መስዋእትነት ተከፍሎ የተገኘውን ነፃነት ማንም ኃይል ጣልቃ ገብቶ “በማንነታችሁ እኔ ልወስን” እንዲል አንፈቅድም ነው ያሉት። ሚዛናዊነት የጎደላቸውና የሕዝብ መከራና በደል ዛሬም ድረስ እንዲያመረቅዝ የሚያደርጉ የፖለቲካ ሽፍጦች በወልቃይት ሕዝብ ላይ እየተሠሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
አንዲት ሉዓላዊት ሀገር አሸባሪ ብላ የፈረጀችውን ቡድን በፖለቲካም ሆነ በሌላ መስክ አባሪም ተባባሪም መሆን አስነዋሪ ተግባር ነውም ብለዋል። አሸባሪውን ትህነግ የመደገፉን እንቅስቃሴ አምርረን እንቃወማለን ነው ያሉት። የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ትብብርን፣ የጋራ ጥቅምንና ሉዓላዊነትን በማስከበርና ማክበር ላይ የተመሠረተ ነው ያሉት አቶ አሸተ የዘመናት ሉዓላዊነት ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ለሚዳፈር ኹሉ ለድርድር አትቀመጥም ብለዋል።
አሜሪካ ሽብርተኝነትን ለመዋጋትና በሌሎች ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር ስታደርገው የቆዬችውን ትብብር ዘንግታ ዛሬ ላይ በተሳሳተ ግምገማ አሸባሪው ትህነግን ለማገዝ የምታደርገው እንቅስቃሴ የተሳሳተ መሆኑን ነው የገለፁት። ትህነግን የሚደግፉ ሀገራት ውሳኔያቸውን እንዲፈትሹትም ጠይቀዋል። በየትኛውም መንገድ ትህነግን መደገፍ ሽብርተኝነትን ማበረታታት መሆኑንም ተናግረዋል።
አሜሪካና አጋሮቿ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ የሚያዩበትን መንገድ እንዲያስተካክሉና የመረጃ ምንጮቻቸውን እንዲፈትሹም ጥሪ አቅርበዋል።
ባለፉት ዓመታት ዓለም ጀሮ የነፈገው ወንጀል በወልቃይት ጠገዴ አማራ ላይ ተፈፅሟል ያሉት አስተዳዳሪው በወልቃይት ጠገዴ የማይካድራ የዘር ማጥፋት ወንጀል አይነት ብዙ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ተፈፅመዋል ብለዋል።
የወልቃይት ጠገዴ አማራ የተነጠቀ ማንነቱን አስመልሷል ብለዋል። “ለውጭ ኃይሎች ልናረጋግጥላቸው የምንወደው የወልቃይት ጠገዴ አማራዎች ያስመለስነው ማንነት እንጂ የነጠቅነው መሬት የለም” ነው ያሉት። የማይገባንን አልፈን አንጠይቅም፣ የራሳችንን አሳልፈን አንሰጥምም ብለዋል። በወልቃይት ጠገዴ ስለተፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጄል የትኛውም ገለልተኛ ነፃ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ማጥናት ቢፈልግ በሩ ክፍት መሆኑንም አስታውቀዋል።
በወልቃይት ጠገዴ የዘር ማጥፋት ወንጄል የፈፀሙ አካላትም በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ጠይቀዋል። በወልቃይት ጠገዴ ለደረሰው በደል ካሳ እንጠይቃለን ያሉት አቶ አሸተ የሞቱትን ባይመልስም ለደረሰው በደልና ግፍ እውቅና እንደሚሆን ነው ያስታወቁት።
ከወልቃይት ጠገዴ የተፈናቀሉ ወገኖች እንዲመለሱ የፌዴራል መንግሥት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር እንዲሠራም ጠይቀዋል።
በወልቃይት ጠገዴ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሰላም መኖር ይችላል፣ የምዕራቡ ዓለም የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ሚዛናዊነት የጎደላቸው ዘገባዎችን ከማሰራጨት እንዲቆጠቡም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ