
በምርት ዘመኑ 131 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማግኘት የሚያስችል የግብርና ግብዓት እየተሰራጨ መኾኑን ቢሮው ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 02/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) በዘንድሮው የመኸር ወቅት የተሻለ ምርት ማግኘት የሚያስችል የግብርና ግብዓት ለአርሶ አደሮች እያሰራጨ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡ በዘንድሮው የመኸር ወቅት በክልሉ ከ4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በሰብል ይሸፈናል፤ በ2013/14 የምርት ዘመን 131 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱንም የቢሮው ምክትል ኀላፊ ተስፋሁን መንግሥቴ ገልጸዋል፡፡
እስካሁንም 554 ሺህ 726 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ነው አቶ ተስፋሁን ያስታወቁት፡፡ ምርትን ለማሳደግ የግብርና ግብዓት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ በተያዘው ዓመት ወደ 7 ሚሊዮን 32 ሺህ 554 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት ታቅዷል፡፡ ይህም ወደ ኢትዮጵያ ከሚገባው 39 በመቶ እንደኾነ አቶ ተስፋሁን ተናግረዋል፡፡
ወደ ክልሉ ለማስገባት ከታቀደው ውስጥ 4 ሚሊዮን 527 ሺህ ኩንታል የቀረበ ሲኾን 3 ሚሊዮን 378 ሺህ 527 ኩንታል የሚኾነው ለአርሶ አደሮች መሠራጨቱን ተናግረዋል፡፡ የከረመ 852 ሺህ 84 ኩንታል መኖሩንም ምክትል ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
ዳፕ የተሰኘው የአፈር ማዳበሪያ አይነት በበቂ ሁኔታ እየተሰራጨ ሲኾን ዩሪያ ደግሞ ወደብ ላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡ ስርጭቱ አርሶ አደሮች ባላቸው መሬት ልክ በመረጃ ላይ ተመስርቶ እየተከናወነ ስለመኾኑም አብራርተዋል፡፡
በክልሉ ወደ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በአሲዳማነት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጎዳ የገለጹት አቶ ተስፋሁን በመኸር ወቅቱ ለመጀመሪያ ጊዜ 200 ሺህ ኩንታል ኖራ ለማቅረብና ለማከም መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡ ኖራ በተለይ ዝናብ በሚበዛበት አካባቢ የተጎዳና የአፈር አሲዳማነትን በማከም ምርትን ሙሉ በሙሉ ያሳድጋል፡፡ እስካሁን ድረስ 46 ሺህ 346 ኩንታል የቀረበ ሲኾን ወደ 13 ሺህ 931 ኩንታሉ ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል፡፡
የክልሉ መንግሥት 272 ሺህ 197 ኩንታል ልዩ ልዩ የሰብል አይነቶች ምርጥ ዘር ለማቅረብ አቅዶ 146 ሺህ 568 ኩንታል አቅርቧል፤ ከ92 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ደግሞ ለአርሶ አደሮች ተሠራጭቷል፡፡
ከዚህ ቀደም የዘር እጥረት ማጋጠሙን ያስታወሱት ምክትል ቢሮ ኀላፊው በተለይ በቆሎ በበቂ ሁኔታ እየተሠራጨ መኾኑን አረጋግጠዋል፡፡ በተወሰነ መልኩ የቢራ ገብስና የስንዴ እጥረት ማጋጠሙን አመላክተዋል፡፡
አልፎ አልፎ የትራንስፖርት ችግር፣ በክልሉ ያጋጠሙ የጸጥታ ችግሮች፣ የኮሮናቫይረስና እየተስተዋለ ያለው የዝናብ መቆራረጥ በዘርፉ ያጋጠሙ ችግሮች ናቸው ተብሏል፡፡ የትራንስፖርት ችግሩን በመፍታት ግብዓቶችን በበቂ ሁኔታ በተገቢው መንገድ ለማቅረብ እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ