በኮምቦልቻ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ የቴክኒክ ትምህርትና ስልጠና ልህቀት ማእከል ፕሮጀክት ግንባታ የማስጀመሪያ መርኃግብር ተካሄደ፡፡

297
በኮምቦልቻ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ የቴክኒክ ትምህርትና ስልጠና ልህቀት ማእከል ፕሮጀክት ግንባታ የማስጀመሪያ መርኃግብር ተካሄደ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 02/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) በመርኃግብሩ ላይ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ፣ የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ሙሉ ነጋን ጨምሮ ሌሎችም የፌዴራል፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በኮምቦልቻ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ የቴክኒክ ትምህርትና ስልጠና ልህቀት ማእከል ፕሮጀክት የሚገነባው በዓለም ባንክ በተገኘ 12 ሚሊዮን 850 ሺህ የአሜሪካን ዶላር የገንዘብ ድጋፍና ብድር ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ለአውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትኩረት በመስጠት ውጤታማ ሥራዎችን ለማከናወን ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ፕሮጀክቱን አስጀምረዋል፡፡ ሚኒስትሩ እንዳሉት ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካትና ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ብሎም የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች መምህራንና አሰልጣኞችን ለማፍራት እገዛ ይኖረዋል፡፡ የገንዘብ ድጋፍ ላደረገው የዓለም ባንክ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ኮምቦልቻን ጨምሮ በሌሎች የሀገሪቱ ሌሎች ሰባት ፕሮጀክቶች የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ የቴክኒክ ትምህርትና ልህቀት ማእከላት እንደሚገነቡ ጠቅሰዋል፡፡
የኮምቦልቻ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን መላኩ አራጋው ይህ ፕሮጀክት በኮሌጁ እየተሰጠ ያለውን የትምህርትና ስልጠና ሥራዎች ለማሻሻልና አዳዲስ ሙያዎችን ለመስጠት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ ዶክተር ከማል ሙሀመድ በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ ለፕሮጀክቱ ግንባታ አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኀላፊዎቹ በኮምቦልቻ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ግቢ ችግኝ ተክለዋል፡፡ በኮምቦልቻ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ የቴክኒክ ትምህርትና ስልጠና ልህቀት ማእከል ፕሮጀክት ግንባታን በአምስት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዟል፡፡
ዘጋቢ፡- ተመስገን አሰፋ – ከኮምቦልቻ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየሚስተዋለውን የነዳጅ እጥረት ለመፍታት በቂ አቅርቦት እንዲኖር እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡
Next articleበምርት ዘመኑ 131 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማግኘት የሚያስችል የግብርና ግብዓት እየተሰራጨ መኾኑን ቢሮው ገለጸ፡፡