
የሚስተዋለውን የነዳጅ እጥረት ለመፍታት በቂ አቅርቦት እንዲኖር እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 02/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች በሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ረጃጅም የተሸከርካሪዎች እና የጀሪካ ሰልፎችን መመልከት የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡ አርሶ አደሮችም ለመስኖ እርሻቸው ማጠጫ ውኃ መሳቢያ ለሚጠቀሙባቸው ጄኔሬተሮች የነዳጅ ፍላጎት እጥረት አጋጥሟቸዋል፡፡ የተሽከርካሪዎች ሥራ ፈትቶ መቆም እና የአርሶ አደሮቹ የመስኖ ሥራቸውን አቋርጠው ነዳጅ ፍለጋ ጀሪካ ይዞ መሰለፍ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል አደለም፡፡
በዚህ ሁሉ መካከል ደግሞ በማደያዎች እና በተጠቃሚዎች መካከል ገብተው የሚደልሉ ደላሎች የማኅበረሰቡ የመልካም አስተዳደር ሳንካዎች ሆነዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ተደጋጋሚ የዘገባ ሽፋን የሰጠው አሚኮ የነዳጅ እጥረቱ በመስኖ እርሻ ሥራቸው ላይ እየፈጠረ ያለውን ጫና በተመለከተ ማደያዎች አካባቢ ወረፋ ይጠባበቁ የነበሩ አርሶ አደሮችን አነጋግሮ እንደ ነበር ይታወሳል፡፡
ከፎገራ ወረዳ በበክስ ቀበሌ ባሕር ዳር ድረስ መጥተው ወረፋ ሲጠባበቁ ያገኘናቸው አርሶ አደር ታደሰ ውባንተ ለመስኖ እርሻ ሥራቸው ነዳጅ ከማደያ መጥፋት የጊዜ፣ የገንዘብ እና ጉልበት ኪሳራ እየደረሰባቸው እንደሆነ ነግረውን ነበር፡፡ ምክንያቱም ውኃው በጄኔሬተር ተስቦ አትክልት ማጠጣት አለባቸውና፡፡ ሌላው ከደራ ወረዳ ዛራ ቀበሌ አሚኮ አነጋግሯቸው የነበሩ አርሶ አደር ገበይ ሰጥአርገው ካሁን ቀደም ነዳጅ በአግባቡ በመቅረቡ ከትንሽ መሬት 80 ኩንታል ሽንኩርት አምርተው ነበር፡፡ በዚህ ዓመት ግን ከ25 ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት እንዳልቻሉ ነግረውን ነበር፡፡ በተለያየ ጊዜ በአቅራቢያቸው ነዳጅ በመጥፋቱ ከነጋዴ ላለመግዛት ባሕር ዳር ቢመጡም ለሌላ እንግልት መጋለጣቸውን በምሬት ነበር የገለጹት፡፡
አሚኮ ለጉዳዩ በሰጠው ትኩረት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችንም አነጋገሮ ነበር፤ ወይዘሮ ወርቃዓለም ኀይለሚካኤል ከደቡብ ወሎ ዞን ጀማ ወረዳ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብት ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በነዳጅ ንግድ ዘርፍ መሰማራት ውጤታማ እያደረጋቸው አለመሆኑን ገልጸውልን ነበር፤ ትርፋማ እንዳይሆኑ ደግሞ የገበያ ሥርዓትና የአቅርቦት ችግሮችን በዋናነት ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት በነዳጅ ዘርፉ ለተሠማሩ ባለሃብቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት ባይ ናቸው፡፡
በማደያዎች አካባቢ በነዳጅ እና ቤንዚን የሚስተዋለው ጥቁር ገበያ ምንጩ ከየት ነው? ችግሩንስ ለመፍታት የክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምን እየሠራ ነው? ሲል የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሚመለከተውን ተቋም አነጋግሯል፡፡ እንደ ሀገር በነዳጅ አቅርቦት ላይ እጥረት አጋጥሟል ያሉት የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊ አቶ አቢታ ገበያው ናቸው፡፡ ከተፈጠረው እጥረት በተጨማሪ የማደያ ባለሃብቶች የገባውን ነዳጅ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የማሰራጨት ችግሮች እንደሚስተዋልባቸው የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊው ጠቁመዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ተደጋጋሚ ጥረት ቢደረግም በመሰረታዊነት ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን ኀላፊው አምነዋል፡፡
በየደረጃው ያሉ አጋር አካላት በተለይም የፀጥታ መዋቅሩ ትብብር አናሳ መሆን እና የንግድ እና ገበያ ልማት መዋቅር ባለሙያዎች በደኀንነት ስጋት ምክንያት በበቂ ሁኔታ አለመሥራት ለችግሩ መባባስ ምክንያት እንደሆኑም ጠቅሰዋል፡፡
በክልሉ በርካታ አካባቢዎች በመስኖ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች እንዳሉ የተናገሩት አቶ አቢታ የሚያለሙት ሄክታር እና የሚያስፈልጋቸው የቤንዚን መጠን በግብርና እና በንግድና ገበያ ልማት ቢሮ መናበብ በኩፖን እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ይህን ሰበብ አድርገው ለጥቁር ገበያው መበራከት ምክንያት የሆኑ አካላት በመኖራቸው ቁጥጥር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ ሕዝብ ግንኙነት ኅላፊው ገለጻ የነዳጅ ወረፋ እንይዛለን እያሉ በየማደያው የገቡ ደላሎችን በተወሰነ ደረጃ ማፅዳት ተችሏል፡፡ በምሽት የሚካሄደውን የነዳጅ እና ቤንዚን ጥቁር ገበያ ለመከላከል ከምሽቱ አንድ ስዓት እስከ ጠዋቱ አንድ ስዓት ከተፈቀደላቸው ተሸከርካሪዎች በቀር እንዳይሸጥ ክልከላ ተላልፏል ብለዋል፡፡ አምቡላንሶች እና የፀጥታ ተሸከርካሪዎች ከሥራዎቻቸው አስቸጋሪነት አንፃር በሌሊትም ቢሆን ሊቀዱ ይችላሉ ነው ያሉት፡፡
ይሁን እንጂ በተለይም በምሽት የሚደረገው ቁጥጥር በበቂ እንዳልተሄደበት እና ችግሮች እንዳሉበት የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊው ገልጸዋል፡፡ ነደጅ የሚገባው በጅቡቲ መስመር መሆኑ እና ክልሉ የሚገባውን ነዳጅ በጥብቅ ክትትል እና ቁጥጥር ከነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች እንደሚረከብ ተናግረዋል፡፡ ይህንን ክትትል ለማምለጥ የተሽከርካሪ ባለሃብቶች እና ሾፌሮች ወደ አማራ ክልል ከመግባት ይልቅ በሌሎች አካባቢዎች መውሰድን የመፈለግ አዝማሚያ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡
የነዳጅ ማደያዎችን እጥረት ችግር ለመፍታት የክልሉ መንግሥት በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ኀላፊው ተናግረዋል፡፡ አሁን የሚስተዋለውን የነዳጅ ጥቁር ገበያ ለመከላከልም በርካታ መጠን ያላቸው ማደያዎችን በየአካባቢው መክፈት እና አቅርቦት ላይ የሚስተዋለውን እጥረት መፍታት ተገቢ እንደሆነ ነው ኀላፊው የጠቆሙት፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ