
ባሕር ዳር፡ መስከረም 8/2012 ዓ.ም (አብመድ) ጊዜው 1968 (እ.አ.አ) ነው፤ በወቅቱ በኬንያዋ የኢኩምቢ መንደር ነዋሪ የነበረው የ30 ዓመት ጎልማሳ በጠዋት ተነስቶ ሰፈሩን ለቅቆ ወጣ፡፡ የትና ለምን እንደሚሄድ ለቤተሰቡ አባላት ሳይናገር ነበር ውልቅ ያለው፡፡
ሰውየው በጠዋት ተነስቶ ከቀየው የተሰወረው ባለቤቱንና ስድስት ልጆቹን ጥሎ ነበር፡፡ ባለቤቷ ድንገት ጥሏት የጠፋው ዋንጂሩ ሙቱ እርሟንም ሳታወጣ፣ ተስፋም አጥታ ለዓመታት በብቸኝነት ልጆቿን ማሳደጉን ተያያዘችው፡፡
ወደቤቱ ከዛሬ ነገ ይመለሳል እያለች ተስፋ ያደረገችው ባለቤቷ ፍራንሲስ ሙቱ ቼግን አንድ ቀን የሆነ አካባቢ ገበያ በሄደችበት መኖሩን ሰማች፡፡ የሌላ ቀን ስንቅ ቋጥራ፣ ሥራዬ ብላ ፈልጋ በአካል ልታገኘው አለ ወደተባለበት ከተማ አቀናች፤ ግን ከዚህችም ከተማ ኮበለለና ጠፋት፡፡
‹‹በዚህ ሁኔታ እንደማላገኘው ተስፋ ቆረጥኩ፤ ባለበት ሠላም እንዲሆን ለፈጣሪ ነግሬ ተውኩት፡፡ አንድ ቀን እንደማየውም ተስፋ ማድረግ ጀመርኩ፡፡ ሙሉ ትኩረቴንም ልጆቼን መንከባከብና ማስተማር ላይ አደረኩ›› ብላለች ዋንጂሩ ሙቱ ለመገናኛ ብዙኃን ስትናገር፡፡
ፍራንሲስ ከሰሞኑ ወደ ቤተሰቡ ተመልሶ ታዲያ ያሳለፈውን ሕይወት ተናግሯል፡፡ በእርግጥ ለምን ቤተሰቡን ጥሎ እንደጠፋ አልተናገረም፤ ነገር ግን ባለፉት 51 ዓመታት ከቤተሰቡ ተነጥሎ ሲኖር ትዳር መስርቶ እንደነበርና ልጅም እንዳፈራ፣ በኋላ ግን ትዳሩ በሱሰኝነቱ ምክንያት እንደተበተነ ተናግሯል፡፡
‹‹ከሰል በማክሰል ሥራ ነው እተዳደር የነበረው፤ የማገኘውን ገንዘብ ግን ሙሉ በሙሉ ለአልኮል መጠጥ አውለው ነበር፡፡ ይህንን ደግሞ ባለቤቴና ልጄ አልተቀበሉትም፤ በዚህም ትዳሬ ፈረሰ፡፡ አሳዛኝ ሕይወት መምራት ቀጠልኩ፡፡ ወደ ቀደመው ቤቴ ለመመለስ ደግሞ አንዳች ነገር አልያዝኩምና አፈርኩ›› ብሏል ፍራንሲስ እንባ እየተናነቀው፡፡
በዚህ ሁኔታ በመጨረሻ ወደ ቀድሞ ቤቱ የተመለሰው የ81 ዓመቱ ፍራንሲስ ልጆቹንና የቀድሞ ሚስቱን አግኝቷል፤ ቤተሰቡና ወዳጅ ዘመድም ድል ያለ ድግስ ደግሰው በደስታ ተቀብለውታል፡፡ ባለቤቷን ለማዬት ተስፋ ያደረገችው እናትም ሕልሟ ተሳክቷል፤ ተስፋን ተስፋ ማድረግ ተስፋ አያስቆርጥምና፡፡
ምንጭ፡- ቱኮ
በአብርሃም በዕውቀት