በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ ያተኮረ ሀገርአቀፍ ጉባኤ በጎንደር ዩኒቨርስቲ ሊካሄድ ነው፡፡

116
በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ ያተኮረ ሀገርአቀፍ ጉባኤ በጎንደር ዩኒቨርስቲ ሊካሄድ ነው፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 02/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታና ዓለም አቀፍ የውኃ ሕጎች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሀገራዊ የምሁራን ጉባኤ ሊያካሂድ መሆኑን የጎንደር ዩኒቨርስቲ አስታውቋል፡፡ ጉባኤው ከነገ ሰኔ 03/2013 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሁለት ቀናት የሚቆይ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስራት አፀደወይን (ዶክተር) እንዳሉት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገንባት ኢትዮጵያን ከድህነት ለመውጣት የምታደርገው ያላሠለሰ ጥረት ማሳያ ነው፤ ግድቡ የኢትዮጵያ የሉዓላዊነት እና የአንድነት መገለጫ ነው፤ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውነታዎች የግንዛቤ ክፍተት ላለባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስተዋወቅ ውይይቱ ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡
በጉባኤው የዓለም አቀፍ የውኃ ሕጎች፣ አለመግባባቶች የሚፈቱበት መንገድ እና ሉዓላዊነትን በተመለከተ ሠፊ ሽፋን የሚሠጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውንም ዶክተር አስራት ከአሚኮ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ ገልጸዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት እንዳሉት ወቅቱ የውጭ ጣልቃ ገብነቶች የተበራከቱበት በመሆኑ የጠራ መረጃ እንዲኖር ለማድረግም ጉባኤው ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
በውይይቱ ላይ በጉዳዩ ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል፤ ከውይይቱም ለመንግሥትም ኾነ ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ የሆኑ ምክረ ሀሳቦች ይገኙበታል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በግብጽ መካከል ያለውን ልዩነት በማጥበብ መፍትሔ ይመላከትበታል ነው ያሉት፡፡
ምሁራን ከውይይቱ ባሻገር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የጠራ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ ተግተው ሊሠሩ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዶክተር አስራት እንዳሉት ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተመለከተ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረጉ ውይይቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፤ መረጃዎችም ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ በውጤቱ ተጠቃሚ እንዳትሆን የውጭ ኃይሎች እንደሚሠሩ እና ይህን ለመመከት በጋራ መቆም እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ውይይቱ ኢትዮጵያ የማንንም ጥቅም ሳትጋፋ የራሷን ጥቅም ለማስከበር እንደምትሠራ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በቂ ግንዛቤ እንዲኖር ለማድረግ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ከውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከሳይንስ እና ከፍተኛ ትምሕርት ሚኒስቴር፣ በዘርፉ ልምድ ያላቸው እና የተለያዩ ጥናት እና ምርምር ያደረጉ አካላት፣ የዩኒቨርስቲ ምሁራን እና ባለድርሻ አካላት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበአማራ ክልል የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እየሠራ መሆኑን የክልሉ አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ፕሮግራም እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገለጸ፡፡
Next articleየሚስተዋለውን የነዳጅ እጥረት ለመፍታት በቂ አቅርቦት እንዲኖር እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡