
“ተውን ነጻነታችንን እናጣጥም” የሑመራ ነዋሪዎች
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 02/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አስተዳደር የሑመራ ከተማ ነዋሪዎች በአሸባሪው ትህነግ ሲደርስባቸው የነበሩ ግፎችንና የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚያወግዝ ሠልፍ በሑመራ እየተካሄደ ነው።
በአሸባሪው ትህነግ አገዛዝ ዘመን የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በደሎች ደርሰውበታል፤ በርካቶች ለህልፈት ተዳርገዋል፣ ከሚኖሩበት ተፈናቅለዋል፣ አካላቸው ጎድሏል። ለዓመታት በዘለቀው የግፍ አገዛዝ ዘመን ወልቃይት ላይ ዓለም ያላዬው ግፍ ተፈፅሟል። ከዓመታት በኋላ በሕዝብ ትግል አካባቢው ከአሸባሪው ትህነግ አገዛዝ ነፃ ወጥቷል። ነፃ በወጡ ማግሥት ታዲያ በሰቆቃቸው የት ነበራችሁ ያላሉ የውጭና የውስጥ ኃይሎች በወልቃይት ጠገዴ ነፃነት ላይ የተለያዩ ሐሳቦችን ማንሳት ጀምረዋል።
የአሜሪካ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የአማራ ልዩ ኃይል ከአካባቢው መውጣት አለበትና ሌሎችን ጥያቄዎችን አንስተዋል። ከዚያም አልፎ በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ የቪዛ ክልከላ ጥለዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ሕዝብ አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች ኃይሎች የሚያነሱት ሐሳብ ያገኘነውን ነጻነት በመንጠቅ ወደ ዳግም ጭቆና ለመመለስ የተደረገ ነው ሲሉ ኮንነውታል፡፡
ለዓመታት ሲገደሉን ዝም ያለ ለወራት ነጻ ስንወጣ መነሳቱ ዓላማው የራስን ጥቅም ማስከበር እንጂ ለሕዝብ አስቦ አይደለም ነው ያሉት።
ነዋሪዎቹ ባካሄዱት ሰልፍ “በማንነታችን ላይ ተናጋሪዎቹ እኛ እንጂ የአሜሪካ መንግሥት ሊሆን አይገባም” ብለዋል።
በሰልፉ ላይ የአሜሪካ መንግሥት እጁን ከወልቃይት ጠገዴ ላይ ያንሳ፣ የአማራ ልዩ ኃይል በወልቃይት ጠገዴ እንጂ ትግራይ ውስጥ የለም፣ የአማራ የግፍ ጥግ ማሳያ ወልቃይት ጠገዴ ነው፣ ዓለም ያልሰማው የዘር ማጥፋት ወንጀል በወልቃይት ጠገዴ አማራ ላይ ተፈፅሟል፣ ወያኔ የፈፀመብን ግፍ ይታወቀልን፣ በማንነታችን አንደራደርም ፣ ከተከዜ ምላሽ ሰውም መሬቱም አማራ ነው፣ በአማራ ልዩ ኃይል፣ በአማራ ሚሊሻና በመከላከያ ሠራዊት ነፃነቴን አግኝቻለሁ የሚሉና ሌሎች መልእክቶች ተላልፈዋል።
ነዋሪዎቹ “ተውን ነጻነታችንን እናጣጥምበት” ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ – ከሑመራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ