
ልዩ ዓላማ ያላቸው የድጎማ ገቢዎች ላይ አሠራር ባለመዘርጋቱ ፍትሐዊ ያልሆነ የመልማት አዝማሚያ ስለሚፈጥር ሊታሰብበት እንደሚገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 01/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ የፓርላማ ዘመን፣ 6ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የምክር ቤቱ የ10 ዓመታት መሪ እቅድ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡ በዚህም ምክር ቤቱ ባለፉት 11 ዓመታት በሥራ ዘመኑ ከማንነት እና ራስን በራስ ማስተዳደር ጋር የቀረቡ አቤቱታዎችን በመፍታት ረገድ ክፍተት በመኖሩ ለግጭት እና ላለመረጋጋት መንስኤ ሆኗል ብሏል፡፡
ምክር ቤቱ ፍትሐዊ የድጎማ እና የጋራ ገቢዎች ማከፋፈያ ቀመር የተጠያቂነት አሠራር አለመዘርጋቱና በፌዴራል አወቃቀር ላይ የጋራ መግባባት አለመደረሱ ለሥራው እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮች ናቸው ብሎ አንስቷል፡፡
ልዩ ዓላማ ያላቸው የድጎማ ገቢዎች ላይ አሠራር ባለመዘርጋቱ ፍትሐዊ ያልሆነ የመልማት አዝማሚያ ስለሚፈጥር ሊታሰብበት እንደሚገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ገልጸዋል፡፡
የምክር ቤቱ የ10 ዓመታት መሪ እቅድ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ እጸገነት መንግሥቱ ገልጸዋል፡፡ የምክር ቤቱ አባላትም የሕገ መንግሥት ይሻሻል ጥያቄ አተያይ፣ የጋራ ማከፋፈያ ቀመር ፍትሐዊነት፣ የሕዝብና ቤት ቆጠራ እና የምርጫ ክልል ክለሳ ላይ ጥያቄ አንስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ልዩ ዓላማ ያላቸዉ የድጎማ በጀቶች ሥርዓት እንዲበጅለት በመሪ እቅዱ እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡ የማንነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች በአፋጣኝ ለመፍታት በክልሎች ወይም በፌዴራል መንግሥት የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታትም ያግዛል ተብሏል፡፡
ምክር ቤቱ የዴሞክራሲያዊ አንድነት የሕገ መንግሥት እና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2013 ዓ.ም የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ተወያይቶ አጽድቋል፡፡
ዘጋቢ፡- ጽዮን አበበ – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ