
የግንደወይን ከተማን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ እንደሚሠራ የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ።
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 01/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚገኙ የከተሞችን የደረጃ ሽግግር የክልሉ ከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ አጥንቶ ባቀረበው መሰረት የክልሉ መሥተዳደር ምክር ቤት ወደ ከተማ አስተዳደር ደረጃ እንዲያድጉ ከተደረጉ ከተሞች ውስጥ አንዷ ግንደ ወይን ትጠቀሳለች፡፡
የግንደ ወይን የከተማ አስተዳደርነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን ተከትሎ ዛሬ የዕውቅና መድረክ ተካሂዷል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አዳነ ተሾመ ባለሀብቶች በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በሌሎችም የልማት መስኮች ከተማዋ ምቹ በመሆኗ አልሚዎች ወደ አካባቢው እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል። የግንደወይን ከተማን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ እንደሚሠራም ከተማ አስተዳደሩ ገልጿል፡፡
የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አያሌው የግንደወይን ከተማ ለኢንቨስትመንት ምቹና ተመራጭ ከተማ እንድትሆን ወጣቶች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የግንደወይን ከተማ ከደጀን ባሕር ዳር ፣ አዲስ አበባ በመርጦለማሪያም መካነሠላም መንገዶች ማዕከል በመሆኗ ለንግድ ተመራጭ መሆኗን የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በከተማ አስተዳደሩ የእውቅና መርኃግብር የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር የሕዝብ ግንኙነትና አደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ እና የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አብርሃም አለኸኝ የግንደወይን ሕዝብ ለሀገር ክብር የቆመ እና የጸና ታሪክ ያለው ሃይማኖቱን የሚያከብር ሠራተኛና ታታሪ ሕዝብ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ሕዝቡ ለልማት፣ ለሰላም እና ለዕድገት ጠንክሮ መሥራት እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡- የኔነህ ዓለሙ – ከግንደወይን
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ