
“ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ማግኘት እንዳለበት ኬኒያ ታምናለች” የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ሪይቸል ኦማሞ
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 01/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ሪይቸል ኦማሞ ጋር በሁለትዮሽ እና በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ በጽሕፈት ቤታቸው ውይይት አድርገዋል።
አምባሳደር ሬድዋን በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ፣ በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር እንዲሁም የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ ለአምባሳደሯ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ቀጣዩ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐሃዊና ተዓማኒ እንዲሆን ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ሆኖ እንዲደራጅ ከማድረግ ጀምሮ ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡ በምርጫው 50 የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወዳደሩ መሆኑን፣ ከሀገሪቱ ለመምረጥ የሚችሉ ዜጎች ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የምርጫ ካርድ ማውጣታቸውን እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ምርጫውን ለመታዘብ መመዝገባቸውን አብራርተዋል።
ኢትዮ-ሱዳን የድንብር ጉዳይን በተመለከተም ሱዳን ወደ ኢትየጵያ ልዑላዊ ግዛት መግባቷንና በኢትዮጵያ በኩል በሀገራቱ መካከል ቀደም ሲል በተቋቋሙ የጋራ ድንብር ኮሚቴዎች አማካይነት በሰላማዊ መንገድ እልባት ሊያገኝ የሚችል መሆኑን ኢትዮጵያ እንደምታምን ገልጸዋል።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር በኢትዮጵያ በኩል በመጀመሪያ የግድቡ የውኃ አሞላልን በተመለከተ ስምምነት ላይ በመድረስ በሌሎች የውኃ ስምምነትን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በተመለከተ ግን ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስዱና የሌሎችንም የተፋሰሱ ሀገራት ተሳትፎ የሚጠይቅ ከመሆኑ አንፃር ቀጥሎ መታየት እንደሚገባው በኢትዮጵያ በኩል የተያዘ አቋም መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ አሁን በአፍሪካ ሕብረት በኩል ድርድሩን በየደረጃው በመክፈል ለማካሄድ የቀረበው ሐሳብ ከኢትዮጵያ አቋም ጋር የሚስማማ ስለመሆኑ ገልጸዋል። ምንም አንኳ ኢትዮጵያ የውኃ አሞላሉን በተመለከተ ከግብጽና ሱዳን ጋር ስምምነት እንዲደረስ ፍላጎት ያላት ቢሆንም እ.ኤ.አ በ2015 በካርቱም በሦስቱ ሀገራት መሪዎች የተፈረመው የመርሆዎች ስምምነት መሰረት የግድቡ የውኃ አሞላል የግንባታው አካል መሆኑን እንደሚገልፅ አስረድተዋል።
የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተም አስፈላጊው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በዋናነት በመንግሥት በኩል እየቀረበ መሆኑ አመላክተዋል። በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተሳተፉ አካላት ተጠያቂ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብዓዊ ተቋም ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር የጋራ ምርመራ እያካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል። አንዳንድ አካላት በክልሉ ተጨባጭ ድጋፍ በማድረግ ገንቢ ሚና ከመጫወት ይልቅ ከእውነት የራቁ እና የተጋነኑ መረጃዎችን በማቅረብ በመንግሥት ላይ ያልተገባ ጫና በማድረግ ላይ መጠመዳቸውን አንስተዋል።
አምባሳደር ሬድዋን ኬንያ እና ኢትዮጵያ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ሰላማዊ ግንኙነት ያላቸው ጎረቤት ሀገራት መሆናቸውን ገልጸዋል። ሀገራቱ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እንዳላቸውና በአትሌቲክስ ተመሳሳይ ጥንካሬ ያላቸው መሆኑን አውስተዋል፡፡ በሀገራቱ መካከል በተለያዩ መስኮች የሚደረጉ ትብብሮች ውጤታማ ለማድረግ ያለውን ምቹ ሁኔታ አስረድተዋል።
በሀገራቱ መካከል በርካታ ስምምነቶች መፈረማቸውም ግንኙነቱ እየተጠናከረ ለመምጣቱ አመላካች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ስምምነቶቹ ያሉበትን ደረጃ በመለየት ተግባራዊታቸውን ማፋጠን እንደሚያስፈልግ እንዲሁም ተጨማሪ የትብብር መስኮችን መጨመር እንደሚያስፈለግ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ወገን በኩል ስምምነቶችን ተፈጻሚ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠውላቸዋል።
የሁለቱ ሀገራት የጋራ የከፍተኛ ኮሚቴ፣ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚቴ እንዲሁም የጋራ የድንበር ኮሚቴ ስብሰባዎችን በሁለቱ ወገን በኩል አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በማጠናቀቅ ማካሄድ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ሪይቸል ኦማሞ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መርህ መሰረት ጉዳዮች እልባት ማግኘት እንዳለበት ሀገራቸው የምታምን መሆኗን ገልጸዋል።
ሚኒስትሯ ኢትዮጵያና ኬኒያ ባላቸው ዘመናት ያስቆጠረ ግንኙነት የተፈራረሟቸውን በርካታ ስምምነቶች ተግባራዊነት በማፋጠን ግንኙነታቸውን የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈለግ ጠቅሰዋል፡፡ በጋራ ጉዳዮች ላይ ሀገራቱ ውይይቶችን በማካሄድ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መምክር እንዲሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የጋራ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ፎረም ማካሄድ እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት የንግድ ምክር ቤቶች መካከል የጋራ የንግድ ምክር ቤት ለማቋቋም የሚረዳውን የጋራ የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሞ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።
የሞያሌ የአንድ መሰኮት ኬላ አገልግሎት በሀገራቱ መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ለማሳለጥ እንዲሁም ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች ለመግታት ካለው ጠቀሜታ አንፃር ወደ ሥራ ማስገባቱ ያለውን አስፈላጊነት ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ እና ኬኒያ በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ይረዳ ዘንድ እስካሁን የተፈረሙ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ተግባራዊነት ለማፋጠን እንዲሁም አዳዲስ የትብብር መስኮችን በመለየት በሁለቱም ወገን በተሰየመ የጋራ ኮሚቴ አማካይነት እንዲቀርብ መግባባት ላይ መደረሱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ