
“የዛሬው ትውልድ ኢትዮጵያን ከውጪም ከውስጥም ጠላት በመከላከል የጀግንነት ታሪኩን ዛሬም እንድትናንቱ እንዲደግም ጥሪ አቅርባለሁ” ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 29/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በማዕከላዊ አርማጭሆ በማሰሮ ደንብ በቀዳሚዊት ጽሕፈት ቤት የሚገነባውን ትምህርት ቤት ሥራ አስጀምረዋል። በሥራ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አርማጭሆ የብዙ የጀግና ሀገር ነው፣ ጀግና ብቻ ሳይሆን ጀግናን የሚወድና የሚያደንቅ ሕዝብ ነውም ብለዋል። ለአብነትም ራስ አሞራው ውብነህን፣ ደጅ አዝማች ብሬ ዘገዬን ፣ ራስ ቢትወደድ አዳነ፣ ራስ ቢትወደድ አዳነንና ሌሎችን አንስተዋል።
የአርማጭሆ ጀግኖች ስማቸው ከምድር በላይ ገኖ የሚነገርና ለልጅ ልጆቻቸው ያለፈ ነውም ብለዋል። አርማጭሆ ጀግና ብቻ ሳይሆን የሚያጀግን ጀግናን የሚያወድስ መሆኑንም ገልጸዋል። የአርማጭሆን ምደር ስለ ስረገጥኩ፣ ውበቱን ስላየሁ ጀግኖችን ስላየሁ ኩራትም ደስታም ተሰምቶኛል ነው ያሉት።
ደጅ አዝማች ብሬ ዘገዬ በስማቸው ትምህርት ቤት የተሰየመላቸው በአርማጭሆ፣ በኢትዮጵያ እና በእንግሊዝ ጭምር ጀግና ስለሆኑ ነውም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። በስማቸው ትምህርት ቤት ቢሠራ ያንስባቸው ካልሆነ በስተቀር አይበዛባቸም ነው ያሉት።
ሁሉም ጀግኖችን በማወደስና ጀግንነት በመሥራት ለልጅ ታሪክ ለማውረስ ትምህርት ቤቱ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡ በአካባቢው ትምህርት ቤት የሚሠራበት ሚሊዮን ጀግኖች እንዲፈጥር ታስቦ መሆኑንም አስታውቀዋል። አርማጭሆ ሲባል ተዋጊ ብቻ አይደለም፣ አርማጭሆ በሞፈርና በምንሽር ነው የሚታወቀው ብለዋል። አርማጭሆ በሠላም ጊዜ አራሽ በክፉ ጊዜ ተኳሽ ነው መሆኑንም ገልጸዋል።
“ስሜን አርማጭሆ የጀግኖች ሀገር፣ እርፍ አገላባጭ እንደዲሞፍተር” የሚባልለት የልማት አርበኛ መሆኑንም አንስተዋል። አርማጭሆ በቀኙ እያረሰ፣ በግራው ሀገር ይጠብቃል፣ ራሱን ማስተዳደር ብቻ ሳይሆን አርበኞችን አምስት ዓመት የደገፈ ጀግና ሠራተኛ ስለሆነም ነው ብለዋል።
አርማጭሆ በመልማትም በጀግንነትም ሀገርን ነው የሚጠብቀው ነው ያሉት። አርማጭሆ መዋጋትና መሥራት ያስተምራል፣ ስንፍና በአርማጭሆ ምድር አይታወቅም፣ ሀገርና መንግሥት ለይቶ የሚያውቅ ጀግና ሕዝብ ነው ብለዋል። የዛሬው ትውልድ ባይመቸውም ሀገር እናት ናትና በምንም ስለማትቀየር፣ በምቾት በድሎት የማትመነዘር በመሆኑ ኢትዮጵያን ከውጪም ከውስጥም ጠላት በመከላከል የጀግንነት ታሪኩን ዛሬም እንድትናንቱ እንዲደግም ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዛሬው ትውልድም ኢትዮጵያን እንዲታደግና ታሪክ እንዲደግም ጥሪ አቅርበዋል። ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው እንዲሉ ወሬ ጀግኖችን ከጀግና ሥፍራ እንዳይውሉ ያደርጋል፣ ወሬ ጀግናን የሚከፋፍል ነውም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚከፋፈል ወሬ ተጠብቆ በአንድነት፣ በፍቅርና በይቅርታ ኢትዮጵያን እንዲያሻግር ጠይቀዋል። መሪዎች አርማጭሆን ሁኑ፣ አርማጭሆ ጀግንነት ብቻ ሳይሆን ትዕግስት ያውቃል፣ መሪዎች እንደ አርማጭሆ ሕዝብ ጀግና፣ ትዕግስተኛ እና ብልሃተኛ ሁኑ ነው ያሉት። ከአርማጭሆ ጀግንነትና ትዕግስት ተምረን ካላሸነፍን የማንገጥም ከገጠምን ግን የማንሸነፍ፣ የማንመለስ መሆናችንን አረጋግጣለሁ ነው ያሉት።
የተወጋን እኛ መልሰን ተወቃሾች እኛ ሆነን እንጂ እውነት ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያውያን ጋር ስላለች አሸናፊ እንደሚያደርገን አልጠራጠርም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አርማጭሆ ጀግኖች ብቻ ሳትሆኑ፣ አጉራሽ፣ አልባሽ፣ ደጋጎች ስለሆናችሁ በትዕግስት ኢትዮጵያውያዊነትን ዳግም እንድታሳዩ አደራ እላለሁም ብለዋቸዋል።
ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m