“ጥራት ያለው የምግብ ዘይት በማምረት በዚህ ዓመት 40 በመቶውን የሐገር ውስጥ ፍላጎት ለማቅረብ እየሠራን ነው” የደብሊው ኤ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለሐብት አቶ ወርቁ አይተነው

476

“ጥራት ያለው የምግብ ዘይት በማምረት በዚህ ዓመት 40 በመቶውን የሐገር ውስጥ ፍላጎት ለማቅረብ እየሠራን ነው” የደብሊው ኤ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለሐብት አቶ ወርቁ አይተነው

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 29/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ማርቆስ ከተማ ከ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው “ደብሊው ኤ” የምግብ ዘይት ፋብሪካ ነገ ይመረቃል።

የደብሊው ኤ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለሐብት አቶ ወርቁ አይተነው የምረቃ ሥነ ሥርዓቱን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ፋብሪካው በሙሉ አቅም ማምረት ሲጀምር የተለያዩ የቅባት እህሎችን በመጠቀም በቀን የጥራት ደረጃውን የጠበቀ ከአንድ ሚሊየን 350 ሺህ ሊትር በላይ ዘይት የማምረት አቅም አለው። በአሁኑ ወቅት ለአንድ ሺህ 500 ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ እንደቻለ የተናገሩት ባለሐብቱ በሙሉ አቅሙ ወደ ማምረት ሲገባ በአንድ ፈረቃ ብቻ ከ3 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጠርላቸዋል ነው ያሉት።

ግዙፍ የምግብ ዘይት ማምረቻው በቀን 18 ሺህ ኩንታል የቅባት እህል ይጠቀማል፤ በዓመትም ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የሚደረግበት 6 ሚሊዮን ኩንታል የቅባት እህል ይጠቀማል ብለዋል።

እንደ ባለሐብቱ አቶ ወርቁ አይተነው ገለጻ በየዓመቱ የሀገር ውስጥ የምግብ ዘይት ፍላጎትን ለማሳደግ በትኩረት ይሠራል፤ ከዚህ ጎን ለጎን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ወደዓለም አቀፍ ገበያ እንደሚያሰራጩም ነው የገለጹት።

ከአራት ዓመት በፊት ግንባታው የተጀመረው “ደብሊው ኤ” የምግብ ዘይት ማምረቻ ፋብሪካ ነገ የፌዴራልና የክልል የሥራ ኀላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ይመረቃል።

ዘጋቢ፡- ስማቸው እሸቴ – ከደብረ ማርቆስ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክት በአካባቢው የመስኖ ልማት ሥራን በማዘመንና የሥራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መኾኑን የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ገለጸ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማዕከላዊ አርማጭሆ ማሰሮ ግንብ ችግኝ ተከሉ፡፡