የጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክት በአካባቢው የመስኖ ልማት ሥራን በማዘመንና የሥራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መኾኑን የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ገለጸ።

161

የጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክት በአካባቢው የመስኖ ልማት ሥራን በማዘመንና የሥራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መኾኑን የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ገለጸ።

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 29/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ ባይነሳኝ ዘሪሁን የጃዊ ወረዳ ማኅበረሰብ የጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክት ለአካባቢው የሚኖረውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በመረዳት ለፕሮጀክቱ መሳካት አስፈላጊውን ኹሉ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ በተለያዩ አስቸጋሪ ጊዜያትም ከፕሮጄክቱ ጎን በመቆም አጋርነቱን አሳይቷል ብለዋል፡፡

ከ4 ሺህ የሚበልጡ ዜጎች መሬታቸወን በመልቀቅ ለፕሮጄክቱ ያላቸውን አጋርነት እንዳሳዩም አብራርተዋል፡፡ ከመሬታቸው የለቀቁ ዜጎችም ትክ መሬት እንዲያገኙና በፕሮጀክቱም ገብተው እንዲሠሩ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ በልማቱ ተነሽ ለኾኑ አርሶ አደሮች የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በማሟላት ነዋሪዎቹን የማስፈር ሥራ ተሠርቷል።

ብሔረስብ አስተዳደሩ በመስኖ ሥራ ይታወቃል ያሉት አቶ ባይነሳኝ የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ በአካባቢው የመስኖ ልማት ሥራን በማዘመንና የሥራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መኾኑን አብራርተዋል፡፡

የጃዊ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አንዱዓለም አቢዩ ነዋሪዎች ለፕሮጀክቱ ሥራ 50 ሺህ ሄክታር መሬት ማስረከባቸውን ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ በአካባቢው በቱሪዝም፣በመስኖ ልማትና በልዩ ልዩ ሥራዎች የሚሠማሩ ባለሃብቶችን እየሳበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፋብሪካው የስኳር ፍላጎትን በማሟላት ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት።

የልማቱ ተነሺና በፋብሪካው ተቀጥረው የሚሠሩት የጃዊ ወረዳ ነዋሪው አበበው አዝመራው ፋብሪካው ለዚህ በመብቃቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል። አርሶ አደሩ በፕሮጀክቱ ተቀጥረው በመሥራት ተጠቃሚ መኾናቸው ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው – ከጃዊ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleብልጽግና ፓርቲ ያዘጋጀው የስድስት ኪሎ ሜትር ሩጫ ውድድር በመስቀል አደባባይ ተካሄደ፡፡
Next article“ጥራት ያለው የምግብ ዘይት በማምረት በዚህ ዓመት 40 በመቶውን የሐገር ውስጥ ፍላጎት ለማቅረብ እየሠራን ነው” የደብሊው ኤ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለሐብት አቶ ወርቁ አይተነው