
የጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፕሮጀክት እውነታዎች
•ፕሮጀክቱ በ2003 ዓ.ም ሲጀመር ሦስት ፋብሪካዎችን ለመገንባት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ዕቅዱ እየተሻሻለ መጥቶ በሂደት አንድ ፋብሪካ ብቻ እንዲገነባ ተደርጓል። የበለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ሥራ ሲጀመር በ18 ወራት ውስጥ ተጠናቅቆ ምርት እንደሚያመርት ዕቅድ ተይዞ ነበር።
•ፋብሪካው በአማራ ክልል ጃዊ ወረዳ ይገኛል። አገዳ የሚለማበት መሬት ግን የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልልንም ያዳርሳል።
•በበለስ ወንዝ ላይ የተመሰረተ የመስኖ መሰረተ ልማት ከ75 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም አለው። የበለስ ወንዝን ተጠቅሞ የሚለማን የሸንኮራ አገዳ በመጠቀም ፋብሪካው የስኳር እና ልዩ ልዩ ተጓዳኝ ምርቶችን ማምረት የሚችልበት ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡
•ዘመናዊ የመስኖ አጠቃቀም ሥርዓትን የሚከተለው ፕሮጀክቱ እስካሁን ከ13 ሽህ ሄክታር በላይ የሸንኮራ አገዳ ማልማት ተችሏል፡፡ ከአገዳ ልማቱ በተጨማሪ በ125 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የፍራፍሬ ልማት ሥራዎችም ተሠርተዋል።
•ፕሮጀክቱ በሀገሪቱ እንደተጀመሩት ሌሎች የስኳር ፕሮጀክቶች ሁሉ ተገቢው የአዋጭነት ጥናት እና በቂ ዝግጅት ሳይደረግለት የተጀመረ ስለነበረ እንደታሰበው ሊሳካ አልቻለም። በ18 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃሉ የተባሉት ሦስት ፋብሪካዎች ይቅርና በስምንት ዓመታት ውስጥ አንዱንም ፋብሪካ እንኳን ማጠናቀቅ አልተቻለም፡፡ የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድም ያን ያህል ፍላጎት አልታየም። ይህም የሆነው በወቅቱ ኮንትራቱን የወሰደው (የቀድሞው የብረታብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን/ሜቴክ) የፋብሪካ ግንባታ የሚያካሂድ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ በነበረው መንግሥት ውሳኔ ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር ትልቅ አቅም የነበረው በመሆኑ ነው።
የፕሮጄክቱ የኮንትራት አስተዳደር ሥርዓትም ሕግን ያልጠበቀ እና በመደበኛው የአሠራር ሥርዓት የማይመራ ነበር፡፡ ኮንትራክተሩም የፋብሪካ ገንቢም፣ ተቆጣጣሪም፣ ባለቤት እና አማካሪ ሆኖ ነበር የሚንቀሳቀሰው፡፡ ከሌሎች የስኳር ፕሮጄክቶች ላይ እንደሆነው ኹሉ ጣና በለስ የስኳር ፕሮጄክት ላይ ከሥራው በፊት ከፍተኛ ገንዘብ ኮንትራክተሩ በቅድሚያ ወስዷል፡፡ ያም ኾኖ የስኳር ልማት ፕሮጄክቶች በአጠቃላይ ትልቅ ችግር ውስጥ መውደቃቸው በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በይፋ መነገር የጀመረው በ2008 ዓ.ም አጋማሽ አካባቢ ነው፡፡ በወቅቱ የፕሮጄክት አስተዳደር ሥራዎችን በሕግ አግባብ ለመምራት ጥረት የተጀመረ ሲሆን በኮንትራክተሩ በኩል ትልቅ ተቃውሞና ማስፈራራት በኮርፖሬሽኑ አመራሮች ላይ ይደርስ ነበር። የአሰሪ፣ የኮንትራክተር እና የአማካሪ የሦስትዮሽ የፕሮጄክት አስተዳደር መዘርጋቱን ተከትሎ አለአግባብ ይከፈሉ የነበሩ ክፍያዎች በመቆማቸው በኮርፖሬሽኑና በኮንትራክተሩ መካከል የነበረው ውጥረት ለይቶለት ይፋ ወጣ። የሜቴክ ችግሮችም እዛም እዚህም ይነገሩ ጀመር፡፡
•በኢትዮጵያ የተደረገው ለውጥ ተከትሎ በፕሮጄክቶች አፈጻጸም ላይ ትልልቅ የማሻሻያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አቅጣጫ በመሰጠቱ የፕሮጄክቱ እጣ ፈንታ የተስፋ ብርሃን ይታይበት ጀመር፡፡ በዚህም የስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ እና ማኔጅመንት በ2010 ዓ.ም ፕሮጀክቱ ከሜቴክ እንዲነጠቅ ተደረገ፡፡ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የፕሮጀክቱን ግንባታ በተለይም በጣና በለስ ቁጥር አንድ ላይ በማተኮር ተጠናቅቆ ለአገልግሎት የሚበቃበትን ሁኔታ ማፈላለግ ዋነኛው የትኩረት ማዕከል ሆኖ ቀጠለ። መንግሥት የተጓተቱ ፕሮጄክቶች ፈጥነው እንዲጠናቀቁ ባሳለፈው ውሳኔ ግንባታውን የተሻለ አፈጻጸም ላላቸው ኮንትራክተሮች በውስን ጨረታ መስጠት የተሻለ አማራጭ ሆኖ በመገኘቱ ይህ አቅጣጫ እንዲተገበር ተደርጓል። በውስን ጨረታ ከተጋበዙት ኮንትራክተሮች መካከል የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክትን የገነባው የቻይናው ሲ ኤ ኤም ሲ ኩባንያ በ95 ሚሊዮን ዶላር ቀሪ ሥራዎችን እንዲያጠናቅቅ በመደራደር ሥራውን እንዲረከብ ተደርጓል።
•በሜቴክ የተጀመረውን ፕሮጄክት ወደ ቻይና ኮንትራክተር የማስተላለፍ ሂደቱ ረጅም እና እልህ አስጨራሽ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። ውሉ ከተሰጠ በኃላ የፕሮጄክቱ ቀሪ ሥራዎችን መለየት እና በዝርዝሩ ላይ መስማማት፣ የተከናወኑ ግንባታዎች ጥራት ፍተሻ ማካሄድ እና በውጤቱ ላይ መግባባት፣ ቀሪ ሥራዎች በሚጠናቀቁበት ጊዜ ላይ ከመግባባት ላይ መድረስ እንዲሁም ሌሎች ሥራዎች ጊዜ የወሰዱ ተግባራት ናቸው ተብሏል።
•መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በ2003ዓ.ም የጣና በለስ ስኳር ፕሮጄክት ሲጀመር ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካ ለማጠናቀቅ የተመደበው ገንዘብ 235 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ነበር። በ2010 ዓ.ም ፕሮጄክቱ ከሜቴክ ሲወሰድ ቀሪ ሥራ እንጂ ቀሪ ገንዘብ አልነበረም፡፡ የቀደመው ኮንትራክተር ለቀጣዩ ኮንትራክተር ግን በርካታ ችግሮችን አውርሶ አልፏል፡፡ ከእነዚህም መካከል በሜቴክ የኮንትራት ዘመን እቃ ለማቅረብ ስምምነት የፈጸሙ ኩባንያዎች ጋር የተያያዘው ችግር ተጠቃሽ ነው። በቀድሞ ኮንትራክተር ዘመን ላቀረቡት እቃ ክፍያ ያልተፈጸመላቸው ኩባንያዎች ከአዲሱ ኮንትራክተር ጋር ለመቀጠል መቸገራቸውን መግለጻቸው በወቅቱ ለፕሮጄክቱ ተጨማሪ ጊዜ መጓተት እንዳይፈጥር ስጋት ያጫረ ሁኔታ ነበር፡፡ ይሁንና ከኩባንያዎቹ ጋር በተደረገ ያላሰለሰ ግንኙነት እና ውይይት ችግሩን በመቅረፍ ፕሮጄክቱን አሁን ለደረሰበት ደረጃ ማብቃት ተችሏል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የኮሮና ቫይረስ በቻይና መታየቱ የተገለጸበት ወቅት ለጣና በለስ የስኳር ፕሮጄክት አስፈላጊ የሆኑ እቃዎች ከቻይና ለማስመጣት ትእዛዝ ከተሰጠበት ወቅት ጋር መገጣጠሙ ፈተና ውስጥ ከትቶ ነበር።
ለፕሮጄክቱ አስፈላጊ የሆኑ እቃዎች በቻይና ፋብሪካዎች ተመርተውና ተጓጉዞ ኢትዮጵያ እንዲደርሱ ማድረጉ ከኮሮና ቫይረስ መከላከያ ፕሮቶኮል አንጻር እጅግ ፈታኝ ሂደት ነበር። በቀጣይም የኮሮና ቫይረስ በሀገር ውስጥ መከሰቱን ተከትሎ በፕሮጄክቱ የሚሠሩ የውጭ ሀገራት ባለሙያዎች ሥራቸውን እያቋረጡ መውጣታቸው፣ ሌሎች ደግሞ በወቅቱ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባት አለመፈለጋቸው ኮሮና በፕሮጄክቱ ላይ ያሳረፈው ሌላኛው ተጽእኖ ነበር። በፕሮጄክቱ የሚሠሩ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችም ለቫይረሱ ተጋላጭ እየሆኑ መምጣታቸው ተጨማሪ ችግር ቢሆንም የኮሮናቫይረስ መከላከያ ፕሮቶኮሎችን ተግባራዊ በማድረግ ችግሩ በፕሮጄክቱ ላይ የከፋ ተጽእኖ እንዳይፈጥር በመደረጉና ቀሪ ሥራዎችን በማጠናቀቅ ለምረቃ ዝግጁ ሆኗል፡፡
የመረጃ ምንጭ፡- ከጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ለምረቃ ከተዘጋጀ መጽሔት የተወሰደ
በአዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m