በጅቡቲ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሄደ።

168

በጅቡቲ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሄደ።

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በጅቡቲ የሚገኘው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ በጅቡቲ ከሚገኙ የእምነት አባቶች፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የመንግሥት ተቋማት ቅርንጫፍ ተወካዮች፣ የኤምባሲው ሠራተኞችና ሌሎች ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ግንቦት 27/2013 ዓ.ም በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂዷል።

በጅቡቲ የኢ.ፌ.ዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋየ በሀገራዊ ለውጡ፣ በትግራይ ክልል በተካሄደው የሕግ ማስከበር ተግባር፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ፣ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር እንዲሁም አሜሪካ በሀገሪቱ ላይ በጣለችው የጉዞ እገዳ ማዕቀብ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

አምባሳደሩ ለሀገራዊ ለውጡ መምጣት ምክንያት የሆኑትን ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ገፊ ምክንያቶች፣ በሀገራዊ ለውጡ የተመዘገቡ ስኬቶችና የገጠሙ ተግዳሮቶች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ ለውጡ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ እየገጠሙ ላሉ ችግሮች ለዘመናት እየተንከባለሉ የመጡ ማነቆዎች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው የሕግ ማስከበር ሥራ መንግሥት ተገዶ የገባበት መሆኑን፣ ህወሀት ሀገራዊ ለውጡ ለማደናቀፍ ህገወጥ ተግባራት ሲፈፅም መቆየቱንና በመጨረሻም በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመሰንዘሩ የፌዴራል መንግሥት የሕግ ማስከበር እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱን ገልጸዋል።

በተወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ህወሃት በአሁኑ ወቅት መደበኛ ሠራዊት የሌለው አሸባሪ ቡድን መሆኑን አውስተዋል፡፡
አምባሳደሩ፣ በትግራይ ክልል በመጀመሪያው ዙር 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች እንዲሁም በሁለተኛው ዙር 2. ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ እንደተደረገላቸው ጠቅሰዋል። ከዚህም ውስጥ 70 በመቶ እርዳታ በመንግሥት እንደተሸፈነ ተናግረዋል።

መንግሥት ከአንድ ሚሊዮን በላይ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡ በክልሉ የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ስለመኖራቸው የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመተባበር ምርመራ እያደረገ መሆኑንና የተጠረጠሩትን ወደ ሕግ የማቅረብ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ አምባሳደሩ ባደረጉት ገለፃ፣ ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ በፍትሐዊነትና በምክንያታዊነት የመጠቀም መርህ እንደምታራምድና ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት በቅርቡ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

ከግብፅና ሱዳን ጋር የሚደረጉ ድርድሮች በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት እንዲቀጥሉ ፅኑ እምነት እንዳላትም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ስላለው የድንበር ጉዳይ ሱዳን የኢትዮጵያን ግዛት መውረሯንና በአርሶአደሮችና በንብረታቸው ላይ ጥቃት መፈፀሟን ኢትዮጵያ ችግሩ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡ የሱዳን መንግስት ግን በሀገር ቤት ባለበት የፓለቲካ ችግር እንዲሁም በሶስተኛ ወገን ግፊት ሳቢያ ፀብ አጫሪነቱ መቀጠሉን ተናግረዋል።

ስደስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በተመለከተ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አምባሳደሩ፣ በአሜሪካ የተጣለው የጉዞ እገዳ ማዕቀብ በተሳሳተ መረጃ ላይ የተወሰደ ውሳኔ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ በራሷ ውስጣዊ ጉዳይ የማንንም ጣልቃገብነት እንደማትቀበል ተናግረዋል፡፡

ክቡር አምባሳደሩ የዳያስፖራ አባላት አንድነታቸውን በማጠናከር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መረጃዎችን ከትክክለኛ ምንጭ በመውሰድ ለሌሎች በማስተላለፍና ለሀገሩ የሚቻለውን ድጋፍ በማድረግ የበኩላቸውን ሀገራዊ ግዴታ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በጅቡቲ ሊገነባ ለታሰበው የማኅበረሰብ ትምህርት ቤት ባለቤት በጀቡቲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ- ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ገልጸው ሁለገብ አስተዋፅኦ በማድረግ የትምህርት ቤቱ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን እንዲሆን መስራት እንደሚገባ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፣ ማንነትም ክብርም ስልጣንም የሚኖሩት ሀገር ስትኖር ስለሆነ ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር የውጭ ጣልቃገብነትን መመከት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ትክክለኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ለሀገራቸው ገፅታ ግንባታ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡ የኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤቱ ግንባታ እውን እንዲሆንም ሁለገብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleለ2013/14 የምርት ዘመን ለመኸር እርሻ የሚውል ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች እየተከፋፈለ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
Next articleየጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፕሮጀክት እውነታዎች