
ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የባሕር ዳር ከተማ የጽጥታ መዋቅር አስታወቀ።
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የጸጥታ ተቋማት ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚያስችል የምክክር መድረክ ዛሬ አካሂደዋል። ሀገራዊ ምርጫው መቃረቡን ተከትሎ ከውስጥና ከውጭ የሚሰነዘሩ ትንኮሳዎች እየተስተዋሉ መኾኑ በመድረኩ ተነስቷል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎችም ትንኮሳዎቹን በማክሸፍ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል። ፖሊስ ሕዝባዊ እና ገለልተኛ ተቋም መሆኑን የገለጹት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ረዳት ኮሚሽነር ከፍዓለ አንዷለም የመራጮች ምዝገባ በሰላም እንዲጠናቀቅ ፖሊስ የድርሻውን ሚና ተወጥቷል ብለዋል፡፡
በምርጫውም ገለልተኛ ኾኖ ሕዝብን እንዲያገለግል የሚያስችል ግንዛቤ መፈጠሩን አመላክተዋል፡፡
የምርጫው ሂደት ሰላማዊ እንዲኾን 394 የፖሊስ አባላት በ179 የምርጫ ጣቢያዎች እንደተመደቡም አስዘንዝበዋል፡፡ “የፈለገውን መምረጥ የሕዝብ መብት ነው፣ የሕዝብን ውሳኔ የማክበር ግዴታ ደግሞ የፓርቲዎች ነው” ያሉት ኮሚሽነሩ የፖሊስ ድርሻ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር ማድረግ መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች መምሪያ ምክትል ኀላፊ አደራ ጋሼ ለከተማ አስተዳደሩ የጸጥታ ተቋማትና አባላት በምርጫ ሥነ ምግባር ሕጉ ላይ ተደጋጋሚ ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
“የጸጥታ ኀይሉ እስካሁን በነበረው የምርጫ ሂደት በጥብቅ ሥነ ምግባር ተልዕኮውን ፈፅሟል፤ ቀጣዩን ሂደትም በገለልተኝነት ሕዝብን ያገለግላል” ብለዋል፡፡
ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሕዝቡ ከጸጥታ ኀይሉ ጎን በመቆምና እንቅስቃሴዎችን እየተከታተለ በመጠቆም የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ