
የችግኝ ተከላ ሳይንሳዊ የአተካከል ሥርዓቱን በተከተለ መንገድ እንዲሆን የደንና የአየር ንብረት ሳይንስ ትምሕርት ክፍል መምሕርና ተመራማሪ ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ ናሽናል ጂኦግራፊ ድረ ገጽ መረጃ ደኖች አሁንም 30 ከመቶውን የዓለምን መሬት ይሸፍናሉ፡፡ ነገር ግን ሽፋናቸው በፍጥነት እየተመናመነ ነው፡፡ በዓለም በየዓመቱ 15 ቢሊዮን ዛፎች ይቆረጣሉ፡፡ እ.አ.አ. ከ1990 እስከ 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ ዓለም 502 ሺህ ስኩዌር ማይል (1.3 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር) ደን እንዳጣች የዓለም ባንክ መረጃ ይጠቅሳል፡፡ ይህም ከደቡብ አፍሪካ አጠቃላይ ስፋት ይበልጣል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 ኔቸር በተባለ መጽሔት ላይ እንደተገለጸው ላለፉት 50 ዓመታት የዓለማችን ግዙፉ ደን አማዞን 17 ከመቶው ተጨፍጭፏል፡፡ ችግሩ እየጨመረ መምጣቱ ደግሞ ስጋትን ፈጥሯል፡፡
የዓለም ሙቀት መጨመር እያስከተለው ባለው ጣጣ አሁንም ለርሃብ እና ተያያዥ ችግሮች እየተጋለጡ ያሉ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ነው፤ በአፈር መሸርሸር፣ በብርቅዬ እንስሳት እና በእጽዋት መመናመን፣ በግብርና ምርቶች መቀነስ፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በመሰል ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ምድሪቱ የደኖችን እርዳታ በእጅጉ የምትሻበት ወቅት ነው፡፡
በአማራ ክልል ብሎም በኢትዮጵያ ችግሩ እየተባባሰ መጥቶ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ሚሊዮኖችን ያሳተፈ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በየዓመቱ እየተከናወነ ነው፡፡ ይህንንም በሥነ ህይወታዊ ዘዴ ለማጠናከር በክረምት ወራት የችግኝ ተከላ ሥራ ቀጥሏል፡፡
ኢትዮጵያም በባለፉት ሁለት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ ቀንን በመሰየም በርካታ ቁጥር ያላቸው ችግኞች ተተክለዋል፡፡ በመንግሥት ተቋማት የሚወጡ ሪፖርቶች እንደሚያመላክቱት ደግሞ ከተተከሉ ችግኞች 80 በመቶ እየጸደቁ ነው፡፡
አማራ ክልል በ2013 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በ182 ሺህ 976 ሄክታር መሬት ላይ 1 ነጥብ 83 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል መዘጋጀቱን የክልሉ ግርና ቢሮ አስተውቋል፡፡ ለዚህም ሁሉም የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የደንና የአየር ንብረት ሳይንስ ትምሕርት ክፍል መምሕርና ተመራማሪ አምሳሉ ንጋቱ ኢትዮጵያ የጀመረችው ተከታታይ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች የደን ሽፋኑን በማሳደግ በደን መመናመን እየደረሰ ያለውን ተጽእኖ ለመቀነስ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ እንደ ምሁሩ ማብራሪያ ለደን መጨፍጨፍ ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም በአየር ለውጥ፣ በአፈር መሸርሸር እና ተያያዥ ችግሮች ምድር ለሰው ልጅ የነበራት ምቹነት እየቀነሰ መጥቷል፡፡ በተከታታይ ዓመታት በሚከሰት ድርቅ ለርሃብ የሚጋለጠው ዜጋ ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ ነው፡፡ መሬቱ በቀጥታ ለዝናብ መጋለጡ በሚከሰት የአፈር መሸርሸር ምርት እቀነሰ ነው፡፡ በተለይ በብዙ ወጪ የሚገነቡ ግድቦች በደለል እየተሞሉ ተገቢው አገልግሎታቸው እየተስተጓጎለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የደን ሽፋን መመናመን የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት ለመቀነስ በችግኝ ተከላ ለማካካስ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ግድ ነው ባይ ናቸው ምሁሩ፡፡ በኢትዮጵያ በተለይ በክረምት ወራት የሚከናወነው የችግኝ ተከላ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋስትና ነው ብለዋል፡፡
ይህንን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በችግኝ ተከላው ሁሉም ሊሳተፍ ይገባል ባይ ናቸው፡፡ ተመራማሪው እንዳሉት ችግኝ ተከላው ለዘመቻ ብቻ ሳይሆን የዘርፉ ባለሞያዎች በሚሰጡት ድጋፍና ምክር ብቻ ሊሆን ይገባል፤ ከተተከሉም በኋላም በባለቤትነት መንከባከብ እና መከታተል እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
ለዚህም ግለሰቦች፣ ተቋማት፣ ማኅበራት እና ሁሉም አካላት በባለቤትነት ኀላፊነት ሊወስዱ ይገባል ባይ ናቸው፡፡ የደን ጉዳይ ሁሉንም ማኅበረሰብ የሚመለከት ቢኾንም የግብርና ተቋማት፣ የጥናትና ምርምር ተቋማት እና ዩኒቨርሲቲዎች በትኩረት ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ