
ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዕድገት የሚዲያ እና ተግባቦት ተቋማት የጎላ ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከተማ ልማት፣ ቤቶች እና ኮንስትራክሽን ቢሮ በክልሉ ከሚገኙ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊዎች እና የሚዲያ ተቋማት ጋር በጎንደር ከተማ ዉይይት እያካሄደ ነዉ። “ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዕድገት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው” በሚል መሪ ሃሳብ ነው ውይይቱ እየተካሄደ የሚገኘው፡፡
የአማራ ክልል ከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ምክትል ቢሮ ኀላፊ አስናቀ ይርጉ በክልሉ በ2008 ዓ.ም 429 ከተሞች እንደነበሩ እና አሁን ቁጥራቸው ወደ 660 ከፍ ማለቱን በዉይይቱ ገልጸዋል። እስከ ቅርብ ጊዜ ሦስት ብቻ የነበሩት ሪጂኦፖሊታንት ደረጃ ያላቸው ከተሞች ቁጥር ወደ ስድስት ከፍ እንዲል መደረጉንም ጠቅሰዋል።
በከተሞች የሚታየውን የቤት እጥረት ለመቅረፍም ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በዋናነት በማኅበር ለተደራጁ የቤት መሥሪያ ቦታ ፈላጊዎች እንደ ክልል ከ200 ሺህ በላይ ዜጎች የቤት መሥሪያ ቦታ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።
ይሁን እንጂ በከተሞች አሁንም ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንደሚስተዋሉ አንስተዋል። በተለይ በትላልቅ ከተሞች የቤት አቅርቦቱ የነዋሪውን ፍላጎት ያሟላ እንዳልሆነ አቶ አስናቀ ይርጉ ጠቅሰዋል፡፡ የሚገነቡ የመሰረተ ልማት ሥራዎች በሚፈለገው ጊዜ፣ በተያዘላቸው የመሥሪያ ዋጋ እና የጥራት ደረጃ እየተከናወኑ አይደለም ብለዋል።
በከተሞች ያለው አገልግሎት አሰጣጥ አሁንም የአገልግሎት ፈላጊውን ፍላጎት ያረካ አይደለም ያሉት አቶ አስናቀ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ እና ሕገ ወጥ ግንባታ እንደተንሰራፋ ነው ብለዋል። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍም እየተሠራ እንደሆነ ነው አቶ አስናቀ ያስታወቁት።
የውይይቱ ዋና ዓላማም የመገናኛ ብዙኃን ማኅበረሰብ የከተማ ልማት ፖሊሲን እና ለቢሮው የተሰጡትን ተልዕኮዎች በውል በመገንዘብ የተከናወኑ ተግባራት ላይ በቂ ሥራ እንዲሠራ ለማስቻል ነው ተብሏል፡፡ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደ አራተኛ የመንግሥት ክንፍ የሚቆጠረው ሚድያዉ በርፉ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለማስቻል እንደሆነ ኀላፊው አስታውቀዋል።
የመንግሥት ተቋማት የሚሠሩትን ሥራ ግንዛቤ ያለው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ከተፈጠረ በቀላሉ ለኅብረተሰቡ መረጃዎችን ማድረስ እንደሚቻል ያስረዱት ደግሞ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ ናቸዉ።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ደረጀ ሞገስ በበኩላቸዉ ሚዲያ እና ኮምዩኒኬሽን ለከተማ እድገት ወሳኝ መሳሪያ መሆቸውን ገልጸዋል። ኮርፖሬሽኑም ለከተማ ልማት ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዉ በቀጣይም ተግባሩ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- አዲስ አለማየሁ – ከጎንደር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ