በሐረሪ ክልል “ስለዓባይ እሮጣለሁ” በሚል መሪ መልዕክት የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ተካሄደ።

109
በሐረሪ ክልል “ስለዓባይ እሮጣለሁ” በሚል መሪ መልዕክት የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ተካሄደ።
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በሐረሪ ክልል “ስለዓባይ እሮጣለሁ” በሚል መሪ ቃል ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ገቢ የሚውል ድጋፍ ለማሰባሰብ የ5 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ተካሂዷል።
በየጎዳና ላይ ሩጫው ላይ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በሐረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የጥናትና ምርምር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኡስማኢል ዩሱፍ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲዳብር ከማስቻሉም በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን በሀገር ጉዳይ ላይ ያላቸውን አንድነት በተግባር ያሳዩበት ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ኢትዮጵያውያን የትኛውንም ግዙፍ ተግባራትን በራሳቸው አቅም መፈፀም እንደሚችሉ ያመላከተ ከመሆኑም ባለፈ ገድቡ መላው አፍሪካውያን መሰል ተግባር እንዲፈፅሙ የሚያነቃቃ ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል።
“ማድረግ የማንችል የሚመስላቸው አካላትም በተግባር ስናሳያቸው ከውጥናችን ሊቀለብሱን የተለያዩ አጀንዳዎችን እየፈጠሩ ከውጥናችን ሊያስተጓጉሉን እየጣሩ ነው” ያሉት አቶ ኡስማኢል፣ ሆኖም እነኚህ አካላት ኢትዮጵያ በማይቀለበስ የብልፅግና ጎዳና ውስጥ መሆኗን መረዳት ይገባቸዋል ብለዋል።
በተለይም ከለውጡ ወዲህ መንግሥት በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዙርያ እያሳየ የሚገኘው ቁርጠኝነት አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመው፣ በቀጣይም ብልፅግና እንደሁልጊዜው ለሀገር ጥቅም፣ ክብር እና ሉአላዊነት ቅድሚያ በመስጠት የሀገራቱን ብልፅግና የማረጋገጥ ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ሕዝቡም የግድቡ ግንባታ እንኪጠናቀቅ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የሐረሪ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት እና በክልሉ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ በበኩላቸው፣ በክልሉ የሚገኘው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዋንጫ በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች እንዲዘዋወር በማድረግ በሕዝቡ ዘንድ ግንዛቤ የማስፋት እና ገቢ የመሰብሰብ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም ሕዝቡ የተጠናከረ ድጋፍ እና ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም ባለፉት ወራት በክልሉ ከወረዳዎች ብቻ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።
በቀጣይም ገቢን የመሰብሰብ እና ግንዛቤን የማስፋት ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ መናገራቸውን ከክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article500 ሽህ ብር ጉቦ በመቀበልና የተለያዩ ሐሰተኛ ስሞችንና ሰነዶችን በመጠቀም ሲያጭበረብር የነበረ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር መዋሉን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
Next articleለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዕድገት የሚዲያ እና ተግባቦት ተቋማት የጎላ ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ፡፡