በቅርቡ የኤሌክትሪክ ኀይል መቆራረጥ መከሰቱን ተከትሎ ለከተማው የመጠጥ ውኃ ለማቅረብ ችግር እንዳጋጠመው የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

118

በቅርቡ የኤሌክትሪክ ኀይል መቆራረጥ መከሰቱን ተከትሎ ለከተማው የመጠጥ ውኃ ለማቅረብ ችግር እንዳጋጠመው የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማ አስተዳደሩ የመጠጥ ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ድረስ አስማረ ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸውም ከሰሞኑ ባጋጠመው የኀይል መቆራረጥ ምክንያት ለከተማዋ ነዋሪዎች የመጠጥ ውኃ ማቅረብ እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡

አቶ ድረስ እንዳሉት ዘጠኝ ጉድጓድ ያለው የጉዶ ባሕር የንጹሕ መጠጥ ውኃ ምንጭ ከግንቦት 19/2013 ዓ.ም ጀምሮ ባጋጠመ የኀይል መቆራረጥ ችግር ምክንያት አገልግሎት መስጠት ተስኖታል፤ በዚህም ቀበሌ 14 ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃና ሕዳሴ ቀበሌ አካባቢ ከፍተኛ የውኃ ችግር ተከስቷል፡፡ ምንጭ ተብሎ የሚጠራው የውኃ መገኛ ከግንቦት 21 ጀምሮ ባጋጠመ ችግር ሙሉ መሀል ከተማው የውኃ ችግር ደርሶበታል ብለዋል፡፡ ስድስት ጉድጓድ ያለው ጨረጨራ ከግንቦት 24 ጀምሮ በመቋረጡ ዲያስፖራና ዘንዘልማ አካባቢዎች ከፍተኛ የውኃ ችግር ተከስቶባቸዋል ነው የተባለው፡፡

የከተማ አስተዳደሩን የውኃ መገኛዎች ለማስተካከል ጥረት ቢደረግም የጨረጨራው የውኃ ተቋም ተመልሶ ብልሽት ደርሶበታል ብለዋል፡፡

የውኃ አቅርቦት ችግሩን በጥቂቱም ቢኾን ለመፍታት አንድ ጉድጓድ በጀነሬተር እንዲሠራ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ አቶ ድረስ የከተማዋ ነዋሪዎች ችግሩ እስከሚስተካከል እንዲታገሱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኤሌክትሪክ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ደግሞ ያጋጠመውን የኤሌክትሪክ ኀይል መቆራረጥ እንዲያስተካክል ጠይቀዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በባሕር ዳር ከተማ ከፍተኛ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር እየታዬ ነው፡፡

ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የመጠጥ ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት በተገኘ መረጃ መሰረት የከተማዋን ነዋሪዎች የመጠጥ ውኃ ፍላጎት ለማሟላት 33 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውኃ ያስፈልጋል፡፡ በሶስት ምንጮች ካሉ 28 የመጠጥ ውኃ ጉድጓዶች የሚገኘው ግን በሰዓት 27 ሺህ 900 ሊትር ብቻ ነው፡፡ ይህም በፍላጎትና አቅርቦት መካከል አለመመጣጠን እንዲፈጠር አድርጓል፡፡

ለችግሩ የኢንዱስትሪዎችና ግንባታ ሥራዎች መስፋፋት፣ የከተማዋ ዕድገት፣ የከተማዋን እድገት ታሳቢ ያደረገ ተጨማሪ የውኃ ጉድጓድ አለመገንባት፣ ሥራ ላይ ያሉት የውኃ መግፊያዎች አቅማቸው እያነሰ መሄድ፣ የመኪና ማጠቢያና የብሎኬት ማምረቻዎች የመጠጥ ውኃን መጠቀማቸው በምክንያትነት ተነስቷል፡፡

አቶ ድረስ በሰጡት መግለጫ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሠራ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም የዘጠኝ የውኃ ጉድጓዶችን ውኃ መግፊያ በአዲስ ለመቀየርና የስድስት ጉድጓዶችን የማምረት አቅም ለማሳደግ ታቅዷል ብለዋል፡፡ የውኃ መሥመር ዝርጋታ ማሻሻያን ጨምሮ ከተማ አስተዳደሩ ለሥራው ወደ 30 ሚሊዮን ብር መመደቡንም ገልጸዋል፡፡

በመገንባት ላይ ያሉ ሁለት የመጠጥ ውኃ ተቋማት ሲጠናቀቁ ችግሩን እንደሚቀንሱት ያስታወቁት ምክትል ሥራ አስኪያጁ ወደፊት አዳዲስ ሰፈሮች ወደ ከተማው ሲካተቱ ተጨማሪ የውኋ ጉድጓድ ቁፋሮ ይካሄዳል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡-ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“የእንስሳት መኖ ታክስ መደረጉ እንደ ግብረና ትክክል አይደለም” የግብርና ሚኒስቴር
Next article500 ሽህ ብር ጉቦ በመቀበልና የተለያዩ ሐሰተኛ ስሞችንና ሰነዶችን በመጠቀም ሲያጭበረብር የነበረ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር መዋሉን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።