“የእንስሳት መኖ ታክስ መደረጉ እንደ ግብረና ትክክል አይደለም” የግብርና ሚኒስቴር

311

“የእንስሳት መኖ ታክስ መደረጉ እንደ ግብረና ትክክል አይደለም” የግብርና ሚኒስቴር

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የእንስሳት መኖ አቅርቦት ችግር በዘረፉ ውጤታማ ሥራ እንዳይሠራ እንቅፋት መፍጠሩን በእንስሳት እረባታ የተሰማሩ ዜጎች ተናግረዋል፡ በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ግብዓት ግብይት ዘርፍ ዛሬ በእንስሳት ግብዓት አቅርቦትና ግብይት ዘርፍ ያሉትን መልካም አጋጣሚዎችን ለማስፋትና ችግሮችን ለመፍታት ዓላማ ያደረገ ውይይት በባሕርዳር ከተማ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡

ኢትዮጵያ በእንስሳት ሃብት ልማት ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር ብትሆንም ባላት የእንሰሳት ሀብት ተጠቃሚ እንዳልኾነች በቅርቡ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን መዘገቡ ይታወሳል፡፡ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝሪያዎችን አለማቅረብ፣ የእንስሳት መኖ ችግርና ለእንስሳት ጤና የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መኾን የዘርፉ ችግሮች እንደኾኑ በውይይቱ በቀረቡ ጥናታዊ ጹሐፎች ተመላክቷል፡፡

በምክክር መድረኩ በእንስሳት እርባታ ሥራ የተሠማሩት ዶክተር ብርሃኑ አድማስ እንደገለጹት በእንስሳት ሀብት ሠርቶ ለመለወጥ ካላቸው ፍላጎት በመነሳት ከመንግሥት ሥራ ወጥተው ወደ ግብርና ሥራ መሠማራታቸውን ተናግረዋል፡፡ በእንስሳት እርባታ ተጠቃሚ የሚያደርግ የግብርና ዘርፍ ቢኾንም የመኖ መወደድና ለእንስሳቱ በቂ የጤና ባለሙያ አለመኖር ለዘርፉ ፈተናዎች መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይም በእንስሳት እርባታ ዘርፍ የተሠማሩ ሰዎች ተጠቃሚ እንዲኾኑ መንግሥት ከእንስሳት መኖ ታክስን ማንሳት አለበት ብለዋል፡፡

በግብረና ሚኒስቴር የእንሰሳትና ዓሳ ሃብት ግብዓት አቅርቦትና ግብይት ዳይሬክተር ብርሃኑ ፈለቀ ሀገሪቱ በተለያዩ ምክንያቶች በእንስሳት ሃብት ማገኘት ያለባትን ጥቅም አለማግኘቷን አስርድተዋል፡፡ ሚኒስቴሩም ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

በእንስሳት ሀብት ልማት የተሰማሩ ዜጎች ከ60 አስስከ 70 በመቶ የሚኾነውን ወጪ ለእንስሳት መኖ ያወጣሉ ያሉት አቶ ብርሃኑ ይህን ችግር ለመፍታት የእንስሳት መኖ ማምረት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት አለበት ብለዋል፡፡ ባለሃብቶችም በሥፋት በመኖ ማቀነባበር ሥራ እንዲገቡ መንግሥት ሰፊ ሥራ እየሠራ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

አርሶ አደሮችም ያልተሻሻሉ ላሞችን ከማርባት በመውጣት የተሻሻሉ የወተት ላሞችን በማርባት ተጠቃሚ የሚኾንበትን አሠራር መከተል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ግብዓት አቀርቦትና ምርት ግብይት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ አይናለም ንጉስ እንዳሉት የእንስሳት እርባታ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡ እንደ ሀገርም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው፤ ከዚህ ቀደም ግብርና ሲባል የሰብል ምርት ላይ ብቻ ትኩረት ሲሰጥ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡

ዘርፉን ለማሳደግ የእንስሳት እርባታውም በቴክኖሎጂ እገዛ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የእንሰሳት እርባታ ሥራን የሚያግዙ አጋር አካላትም በስፋት ወደ ሥራው እየገቡ እንደኾነ ወይዘሮ አይናለም ተናግረዋል፡፡

ዝርያን ለማሻሻል ኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂ አቅሙን እያሳደገ ነው ብለዋል፡፡ በሂደት በሀገሪቱ የሚገኙ የእንሰሳት አርቢዎች ያልተሻሻሉ የእንሰሳት ሀብታቸውን ቁጥር እየቀነሱ የተሻሻሉ ዝሪያዎችን እንዲጠቀሙ በትኩረት እንደሚሠራም አስረድተዋል፡፡

የእንስሳት ጤናን ለማሻሻል በሀገር ውስጥ የእንስሳት ክትባትና መድኃኒት የማምረት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

“የእንስሳት መኖ ታክስ መደረጉ እንደ ግብረና ትክክል አይደለም” ያሉት ሚኒስቴር ዲኤታዋ አሠራሩን ለማሻሻል የሚያስችል ጥናት ተጠንቶ ተጠናቋል፤ በቀጣይም ዘረፉን ለሚያስተዳድርው አካል ይቀርባል፤ የጥናቱ ውጤት ሲቀርብም ውሳኔ የሚሰጠው ይኾናል፤ ችግሩም የሚፈታ እንደኾነ አብራርተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበክልሎች የጎርፍ አደጋን ለመከላከል 300 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ወደ ሥራ መገባቱን የኢትዮጵያ ተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
Next articleበቅርቡ የኤሌክትሪክ ኀይል መቆራረጥ መከሰቱን ተከትሎ ለከተማው የመጠጥ ውኃ ለማቅረብ ችግር እንዳጋጠመው የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡