
“እውነት ይዛ ሰሚ፣ ሀቅ ይዛ ተቀባይ ላጣችው የአሁኗ ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ፍቱን መድኃኒት ነው” የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ የሚጀምረው ዘመነ መሳፍንት አክትሞ አፄ ቴዎድሮስ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጀምሮ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ለበርካታ ሽህ ዓመታት ድንበሮቿን በአራቱም አቅጣጫ ለቀሪው ዓለም ዝግ አድርጋ የዘለቀችው ኢትዮጵያ ቀስ በቀስ ለውጭ ግንኙነት ራሷን ክፍት ማድረግ ጀመረች፡፡ የውጭ ስልጣኔን አጥብቀው ይሹ የነበሩት አፄ ቴዎድሮስ ከሞላ ጎደል ከውጭ ነገሥታት እና መንግሥታት ጋር በትብብር የመሥራት ፍላጎት አሳይተው እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡
ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ ንግሥና ማክተም በኋላም የመጡት ነገሥታት የውጭ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ወቅቱ እንደሚፈልገው መጠን እና አቅማቸው በፈቀደ ልክ ለመመስረት ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን ይፋዊ የሆነውን የምዕራቡ ዓለም ዲፕሎማሲ መሬት ያስነኩት ዳግማዊ ምኒልክ ነበሩ፡፡ በ1900 መባቻ “ጥቁሩ ንጉሥ” እየተባሉ የሚሞካሹት የአድዋ ድል መሪ ዳግማዊ አፄ
ምኒልክ ከሚመሯት ምሥራቅ አፍሪካዊት የነፃነት ተምሳሌት ሀገር ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መመስረት ሻተች፡፡ ከበርካታ ሂደቶች በኋላ የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመመስረት ፍላጎት ሰምሮ (እ.አ.አ) ታኅሣሥ 27/1903 አንድ ብሎ ጀመረ፡፡
ከአፄ ምኒልክ እረፍት በኋላ በልጅ እያሱ እና በንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ ተዳክሞ የነበረው የውጭ ግንኙነት 1923 ዓ.ም ወደንጉሠ ነገሥትነት ዙፋን የዘለቁት አፄ ኃይለሥላሴ ገና በአልጋ ወራሽነታቸው ዘመን እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1923 ወደ ዓለም ሀገራት ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽን) በመቀላቀል የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ሰቀሉት፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ ንጉሡ የዓለም ሀገራት ማኅበር በጥቅምት 3/1935 (እ.አ.አ) በጣሊያን የተጀመረውን ዳግማዊ ጠብ አጫሪነት ይከላከልልኛል የሚል ተስፋቸውን ቢያጨልመውም ከድል ማግስት የነፃ ሀገርነትን ቦታ ግን አሰጥቷታል፡፡
የንጉሠ ነገሥቱ ብስለት እና የውስን ቆንሲሎቿ ጥረት ኢትዮጵያን በ1950ዎቹ ወርቃማ የዲፕሎማሲ ዘመን እንድታሳልፍ እንደረዳትም ይነገራል። የኤርትራ የፌዴሬሽን ውሕደት እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ስኬት የንጉሠ ነገሥቱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ውጤት ተደርጎም ይወሰዳል፡፡
ከቀይ ባሕር እስከ ሕንድ ውቅያኖስ ያለውን አካባቢ የመቆጣጠር ፅኑ ፍላጎት የነበራቸውን የምዕራባውያን ሀገራት ሴራ ተቋቁመው፣ በዓባይ ውኃ ላይ የዘመናት መሻት የነበራትን ብሪታኒያን እና ቅኝ ተገዥ አሽከሮቿን ሴራ ችለው ጃንሆይ አፍሪካዊ አስተሳሰብ ስር እንዲሰድ በብርቱው ሠሩ፡፡
የትናንቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ የዛሬው የአፍሪካ ሕብረት ግንቦት 16/1955 ዓ.ም ሲመሰረት የድርጅቱ ታሪካዊ የብኩርና ሊቀመንበር የሆኑት አፄ ኃይለሥላሴ እና የምንጊዜም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መዲና የሆነችው አዲስ አባባ በዓለም አደባባይ ላቅ ያለ የዲፕሎማሲ ካባን ተጎናፀፉ፡፡
ከአፍሪካ ሀገራት በተለየ ይህን መሰል ላቅ ያለ የዲፕሎማሲ እምርታ ማስመዝገብ በእርግጥም የተለየ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጥበብን ይጠይቃል፡፡ ከብሔርተኛው ናስር እስከ ንኩሩማ፤ ከኔሬሬ እስከ ሴኮቱሬ፤ ከሴንጎር እስከ ኬኒያታ ተለይተው ንጉሡ በአፍሪካ ላቅ ያለ የመሪነት ቦታ ተቸራቸው፤ ኢትዮጵያም የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት ተደርጋ ተወሰደች፡፡ ይህ ምትሐታዊ ተዓምር ሳይሆን የንጉሡ ጥረት፣ የከተማ ይፍሩ ታታሪነት፣ የአክሊሉ ሃብተወልድ ብስለት እና የአጋሮቻቸው ጥረት ውጤት ነው፡፡
ከዘውዳዊው የንጉሠ ነገሥቱ የስልጣን ዘመን ማክተም በኋላ ወደ መንግሥትነት ርካብ የመጣው ወታደራዊ ደርግ ዘመናዊ የመንግሥት አሥተዳደርን እንዳስተዋወቀም ይጠቀሳል፡፡ በዲፕሎማሲው መስክ ግን ዳፋው ለዘመናት የዘለቀ ሳንካን በሀገሪቱ ላይ ቀርቅሮ እንዳለፈ የሚያምኑት በርካቶች ናቸው፡፡ ወደ መንበረ መንግሥትነት እንዲመጣ የአሜሪካ ስውር እጆች ረድተውታል የተባለለት የመንግሥቱ ኃይለማርያም ወታደራዊ አገዛዝ ከአሜሪካ ጋር የነበረው ሽርክና ግን ከሦስት ዓመታት በላይ አልዘለቀም የሚሉት ይበዛሉ፡፡
ታላቋን ሶማሌ ላንድ የመመስረት የቆየ ፍላጎት የነበረው ዚያድ ባሬ በምሥራቅ ኢትዮጵያ በኩል መጠነ ሰፊ ጦርነት መክፈቱ ከሌሎቹ የገንጣይ ተገንጣይ ቡድኖች የህቡዕ መሻት ጋር ተዳምሮ መንግሥቱን ረዳት ፍለጋ የርዕዮተ ዓለም እስረኛ አደረጉት፡፡ ከምዕራቡ ዓለም ሀገራት ፓለቲካዊ እሳቤ በተፃራሪ ከቆሙት ሶቪየት ሕብረት እና ኩባ ጋር የጠበቀ ዝምድናን ፈጠረ፡፡
በዚህም በምዕራባውያን ጥርስ ውስጥ የገባው የመንግሥቱ ኃይለማርያም መንግሥት በተለይም በአሜሪካ መንግሥት ለሚደገፉት የገንጣይ አስገንጣይ ቡድኖች ሰርግና ምላሽ ሆነላቸው፡፡ ከስር ከስሩ ሲቦረቦር የነበረው የደርግ ሥርዓት ወደቀ፡፡
ከደርግ መውደቅ በኋላ ወደ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት የገባው ኢሕአዴግም ጫካ ውስጥ እያለ ይምል ይገዘትበት የነበረውን የማኅበረ ሱታፊ አቀንቃኝነት ካባው አውልቆ መርሕ አልባውን የዲፕሎማሲ እና የውጭ ግንኙነቱን ጉዞ አንድ ብሎ ጀመረ፡፡ በዘመነ ኢሕአዴግ በሀገር ብሔራዊ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲ አልነበረም እየተባለ በዘርፉ ምሁራን ይተቻል፡፡ የሀገሪቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተመሰረተው በቡድን እና በግለሰቦች ጥቅም ላይ ተመስርቶ እንደነበር ይነገራል፡፡
የዘመነ ኢሕአዴጉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አሁን ድረስ ሲወርድ እና ሲወራረድ ለመጣው ሀገራዊ የውጭ ግንኙነት ችግር መነሻም መድረሻም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ከለውጡ በኃላ ስልጣን የመጣው መንግሥት ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን ከማከናወን አኳያ ሰፊ ሥራዎች እንደሚጠይቁት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምሕርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር በዕውቀቱ ድረስ (ዶክተር) ገልጸዋል፡፡
አሁን የሚስተዋሉት ውስጣዊ እና ቀጣናዊ ችግሮች የወለዱት የውጭ ሀገራት የበዛ ጣልቃ ገብነት ኢሕአዴግ በ27 ዓመታት በዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና በታዋቂ ግለሰቦች የሰገሰጋቸውን አጥፊ ኃይሎች ለማጋለጥና ያለውን ትክክለኛ ገጽታ ለማሳወቅ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ መሥራት ያሰፈልጋል ነው ያሉት።
እውነት ይዛ ሰሚ፣ ሀቅ ይዛ ተቀባይ ላጣችው የአሁኗ ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ፍቱን መድኃኒት ነው የሚሉት ምሁሩ ለዚህ ደግሞ ዘርፉ ስር ነቀል ለውጥ ይሻል፡፡ ለዚህም ከዲፕሎማቶች ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ተጨማሪ ማጣቀሻ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦፍ ብሪታኒካ
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ