
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በውጭ ሀገራት የማሰራጫ ስቱዲዮ እንዲኖረው ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው ሙሉቀን ሰጥዬ ገለጹ።
ሚዲያው በውጭ ሀገራት የዘገባ ሥራ ለመሥራትና የራሱን የማሰራጫ ስቱዲዮ ለመክፈት በሚያደርገው ጥረት ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) መነሻን ከበኩር ጋዜ አድርጎ፣ በዓመታት ቅብብሎሽ አድጎ፣ ኢትዮጵያን እያካለለ፣ ዓለምን ሊያዳርስ ሥራ ላይ ነው። ኩሩ ሕዝብ መነሻ ቤቱ፣ መተዳደሪያ ባለቤቱ የሆነው የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የአማራን እና የመላው ኢትዮጵያን ሕዝብ እውነተኛ ታሪክ፣ ለእውነተኛ ሕዝቦችና ሀገሮች ለማድረስ ጥረት እያደረገ ነው። ማተቡ ክብሩ፣ ጀግንነት የዘሩ፣ አስታዋይነት ምግባሩ አርቆ አሳቢነትና ኢትዮጵያዊነት የደም ሥሩ የሆነው የአማራ ሕዝብ የወለደው፣ ተንከባክቦ ያሳደገው፣ እየደገፈ ያራመደው ነው የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን።
ቀን ቀንን ሲተካ ዓመታት ሲቀባበሉ አሚኮም በዓመታቱ ፍጥነት፣ በሰዎች ፍላጎት፣ በዘመኑ ሂደት ልክ ራሱን እያሻሻለ እድገት ላይ ነው። አሚኮ በኢትዮጵያ ተመርጦ የሚደመጥ፣ እውነተኛ መረጃን ለሕዝብ የሚሰጥ፣ እውነተኛውን የኢትዮጵያውያንን ታሪክ የሚገልጥ ሚዲያ ነው። መርጠው ያዳምጡታል፣ ወደው ይመለከቱታል፣ ተከታትለው ይረኩበታል፣ ዘመንን ይዋጁበታል። በኢትዮጵያ ከሚገኙ ታላላቅ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚመደበው አሚኮ ዘመኑን እየዋጄ ራሱን ለማሳደግ የሚያደርገውን ጎዞ የበለጠ በማፍጠን ላይ ነው።
አሚኮ የአማራ ክልልን እያዳረሰ፣ ኢትዮጵያን እየዳሰሰ፣ ዓለምን ሊቃኝ ጉዞ ላይ ነው። አሚኮ በኢትዮጵያ ብሎም በምሥራቅ አፍሪካ ግዙፉ የሚዲያ ተቋም ለመሆን የሚያደርገውን ራዕይ እውን ለማድረግ በውጭ ሀገራት የራሱን የማሠራጫ ጣብያ ለመክፈትም ሥራ ላይ መሆኑ ተገልጿል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሙሉቀን ሰጥዬ ሚዲያው የአማራን ሕዝብ እውነተኛ ታሪክ ለማድረስና ለመግለጥ እገዛ እንደሚፈልግ ተናግረዋል። ሚዲያውን ለማሳደግ ሁሉም ኅብረተሰብ አስታያየት መስጠት እንደሚገባውም ገልጸዋል። አቅሙ ያላቸው አካላት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባቸውም ጠይቀዋል። ከሚዲያው ጋር እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከኢትዮጵያ አልፎ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው በተመረጡ የውጭ ሀገራት የዘገባ ሥራዎችን ለመስራት በሂደት ላይ ነው፣ ቀስ በቀስም የራሱን ስቱዲዮና የማሰራጫ ጣብያ እንዲኖረው ለማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ዋና ሥራ አስፈፃሚው አስታውቀዋል።
በውጭ ሀገራት የሚኖረውን የወኪል ዘጋቢዎቻን በማደራጄት፣ በመምረጥና በመሳተፍ ራሱን እያሳደገ ሲሄድ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ከኢትዮጵያ ጋር መገናኛ ድልድይ ሆኖ እንዲያገለግላቸው ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚጠይቅም ገልፀዋል። ከአሚኮ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ሥራዎች እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
ለኢትዮጵያውያን የሀገራቸው የልማት አቅም መሆን እንዲችሉ፣ የአማራ ክልልን ብሎም ኢትዮጵያን በሁሉም ዘርፍ ማገዝ የሚቻሉበትን ዘዴ ሚደያው መንገድ ቀይሶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ተናግረዋል። አሚኮን ለማገዝና በተመረጡ የውጭ ሀገራት ከተሞች ሥራ ለማስጀመር የሚደረገውን ጥረት ሀሰብ በማመንጨትና በልዩ ልዩ ጉዳዮች የማገዝ ፍላጎት ካላቸው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር ሚዲያው በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ባሉበት ሆነው አሚኮን የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ትልቁ ሚዲያ ለማድረግ የተጀመረውን ጉዞ እውን ለማድረግ በቴክኖሎጂ፣ በይዘት፣ በአሠራር፣ በአቀራረብ፣ በሀብት አሰባሰብና ሚዲያን ለማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ሁሉ እንዲያግዙም አቶ ሙሉቀን ጥሪ አቅርበዋል።
አሚኮ መነሻውና ባለቤቱ የአማራ ክልል ሕዝብ ቢሆንም የባለቤትነት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ፣ የክልሉ ሕዝብና የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መስተጋብር ማሰደግ ስለሚገባ፣ የተሳሳተ ትርክትን በማረምና እውነተኛ የሆነ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲፈጠር የመሥራት ሕዝባዊ ኃላፊነት አለበትም ብለዋል።
አሚኮ በቅርቡ ሁለተኛ የቴሌቪዥን ስርጭት እንደሚያስጀምርም አስታውቀዋል።
ሚዲያው የጋራ ሀብት ስለሆነ በጋራ ማሳደግ ይገባልም ነው ያሉት። አሚኮ በዘርፉ ለኢትዮጵያና ለሚዲያ ተቋማት ታላቅ ግልጋሎት የተሰጠ ታላቅ ተቋም መሆኑንም አንስተዋል።
ተቋሙ ራሱን በየጊዜው እያሳደገ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ለመጥቀም ሥራ ላይ ነው። ሚዲያውን በሀገሪቱ ተመራጭ ለማድረግ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ነው ሥራ አስፈፃሚው የገለፁት።
አሚኮ ፍላጎት፣ ፍጥነት፣ የሥራ ተነሳሽነትና ሕዝባዊ ወገንተኝነት ያላቸው ባለሙያዎችን የያዘ ተቋም መሆኑ ይታወቃል፤ ሲታገዝም ጠንካራ ሀገርና ሕዝብ መፍጠር ያስችላል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ