በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ዘመናዊ የፎረንሲክ ሰነድ ማጣሪያ ላቦራቶሪ ስራ ጀመረ።

94

በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ዘመናዊ የፎረንሲክ ሰነድ ማጣሪያ ላቦራቶሪ ስራ ጀመረ።

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 26/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የፎረንሲክ ላቦራቶሪው የተገኘው ዓለም ዓቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) እና የጀርመን መንግስት ለኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ባደረጉት ድጋፍ ነው።
ላቦራቶሪው የተጭበረበሩ የጉዞ ሰነዶች፣ ፓስፖርት፣ ቪዛና ሌሎችንም ዶክመንቶች በቀላሉ መለየት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

የዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሙጂብ ጀማል ከዚህ በፊት የጉዞ ሰነዶች የሚረጋገጡት በአይን በማየት ብቻ መሆኑን አስታውሰው፤ “ላቦራቶሪው በየዘመኑ እየተለዋወጠ የመጣውን የወንጀለኞችን እንቅስቃሴ ለመግታት ያግዛል” ብለዋል።
ዘመናዊ የጉዞ ሰነድ ማጣሪያው የአሸባሪዎችንና የሕገ ወጦችን እንቅስቃሴ ለመግታት የቁጥጥር አሰራሩ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።

በድጋፍ የተገኙት የፎረንሲክ ላብራቶሪዎቹ ከ5 እስከ 7 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ሲሆን ሁለቱ በቦሌ አየር ማረፊያ ተተክለው ዛሬ ስራ ጀምረዋል።
“አንዱ ላቦራቶሪ ደግሞ በዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና መስሪያ ቤት ለማሰልጠኛነት ተገጥሟል” ብለዋል።

በተለይም ኢ-ፓስፖርት የሚጠቀሙ ዓለም ዓቀፍ ተጓዦችን አጠቃላይ ሁኔታ በቀላሉ ለማወቅ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በዓለም ዓቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ልኡክ ሃላፊ ማውሪን አቼንግ “የላቦራቶሪ ማሳሪያው መረጃዎችን በማጣራት ሕገ ወጥ ስደትን ለመቆጣጣር ትልቅ ፋይዳ አለው” ብለዋል።

ሕገ-ወጥ ስደተኞች የሚይዙትን ሰነድ ትክክለኛነትና አጠቃላይ ማንነት በቀላሉ ማረጋገጥ ስለሚቻል የሰዎችን ዘላቂ ደህንነት ለመጠበቅም ይረዳል ነው ያሉት።
ከዚህ ባሻገር በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣ የጸጥታ አደጋና ስጋት ካለ ቀድሞ ለመከላከልም ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

ከማሽን ተከላው በተጨማሪ ሙያተኞችን ያሰለጠነው የጀርመን መንግስትን የወከሉት በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አወር የላቦራቶሪ መሳሪያው ጥቅም በርካታ መሆኑን ገልጸዋል።

“እየጨመረ ካለው የተጓዦች ቁጥር አንጻር ትክክለኛ ያልሆኑ የጉዞ ሰነዶችን ከጥቅም ውጪ ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል።
የጀርመን መንግስትም በዚሁ መነሻነት ኢትዮጵያን ለመደገፍ መነሳቱን አምባሳደሩ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleከሰላማዊ ዜጎች ግድያና ከጾታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ በ53 የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ክስ ተመሰረተ።
Next articleኮሚሽኑ ከ700 ሺህ ኩንታል በላይየምግብ ድጋፍ ወደ ትግራይ መላኩን አስታወቀ።