
ለአምባሳደሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች በትግራይ ክልል እየተከናወኑ ስለሚገኙ ስራዎች ገለጻ ተደረገ፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 26/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲስ አበባ ለሚገኙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ድጋፍ አቅራቢ ተወካዮች በትግራይ ክልል መንግስት እያከናወናቸው ስለሚገኙ ስራዎች ሰፊ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በጤና፣ ትምህርት ዘርፍ እና በተለያዩ መስኮች መንግሥት የአቅሙን ያህል ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ሥራውን የሚደግፉ ሰብአዊ ድጋፍ አቅራቢ ተቋማት እንዳሉ ሁሉ ግን ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት የፖለቲካ ጨዋታ የሚያካሂዱ መኖራቸውንም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መረዳት እንዳለበት ተናግረዋል።
አሁን ላይ በትግራይ ከሚገኙ ጥቂት ችግር ያለባቸው ሁለት አካባቢዎች በስተቀር በአብዛኛው ቦታ ከጦርነት ነጻ የሆነ እንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑን የተናገሩት አቶ ደመቀ፤ አብዛኛው የትግራይ ክልል አካባቢ ግን የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት የተመቻቸ በመሆኑ የተለያዩ ድጋፎች እንዲጠናቀሩ ጠይቀዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አብረሃም በላይ በበኩላቸው በትግራይ ክልል የተረጋጋ እንቅቃሴ እንዲኖር መጠነ ሰፊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን እና ጥረቱን ለመደገፍ ግን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢ ተቋማት ሰፊ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በጊዜያዊ መጠለያ አቅርቦት፣ በጤና፣ ትምህርት እና የንጽህና ግብዓት አቅርቦት ላይ በሰፊው በመሰማራት የትግራይን ሕዝብ ችግር ሊቀርፉ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ደግሞ፤ በክረምቱ ወቅት የግብርና ሥራ እንዲከናወን የግብርና አቅርቦት እየቀረበ መሆኑን እንዲሁም ባንኮችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት በአብዛኛው ስራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።
የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ ክፍያቸውን ተቀብለው በመስራት ላይ መሆናቸውን እና በመቀሌ የሚገኝ የግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ግብር መቀበል መጀመሩን ተናግረው፤ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የጤና የትምህርት እና ሌሎች ዘርፎች መነቃቃት ማሳየታቸውን ለአምባሳደሮቹ አስረድተዋል።
በመድረኩ የመከላከያ ሚኒስቴር እና የተለያዩ የጸጥታ አካላት ሃላፊዎች፣ የግብርና ሚኒስቴር እና የብሔራዊ አደጋ ስጋት መከላከልና መቆጣጠር ኮሚሽን እንዲሁም የተለያዩ የመንግስት ኃላፊዎች ተገኝተው ለአምባሳደሮች እና ለዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች በትግራይ እየተከናወኑ ስለሚገኙ ሥራዎች ገለጻ አድርገዋል። ኢፕድ እንደዘገበው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ