
“ፕሮፐርቲ 2020” ኩባንያ በአዲስ አበባ ከተማ 100 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ስምምነት ወሰደ።
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 25/2013 ዓ.ም (አሚኮ) “ፕሮፐርቲ 2020” የተባለው የደቡብ አፍሪካ በቤት ልማትና ግንባታ ዘርፍ የተሠማራው ኩባንያ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 100 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ስምምነት ወስዷል። ኩባንያው በመዲናዋ ያለውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና እና ጥያቄ በመመለስ በኩል ሚናው የጎላ እንደሚሆን ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።
ኩባንያው በመጀመሪያው ዙር 100 ሺህ ቤቶችን የሚገነባ ሲሆን በመጭዎቹ 5 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ደግሞ 500 ሺህ ቤቶችን ይገነባል ተብሏል። ይህም በከተማዋ ያለውን የቤት ፍላጎትና አቅርቦት ያለውን ከፍተኛ አለመመጣጠን ለመቅረፍ ያሥችላል ተብሏል።
ፕሮጀክቱ ለከተማዋ ብሎም ለኢትዮጵያ ወጣቶች የኮንስትራክሽን ተመራቂዎች ከፍተኛ የሥራ እድል እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ይፈጥራል ነው የተባለው።
4 ነጥብ 1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጭ የሚጠይቀውን የቤቶች ግንባታ ለመከወን የከተማ አስተዳደሩ መሬት በነጻ ለማቅረብና መሠረተ ልማት ለማሟላት የወሰደውን ተነሳሽነት ያደነቁት ኩባንያውን ወክለው ንግግር ያደረጉት ኢንጅነር ጃርሶ ጎሊሶ ናቸው፡፡
ኩባንያው ዓለማቀፍ ልምድን ያካበተ በመሆኑ ቤቶችን በተያዘለት ጊዜ በጥራት ገንብቶ ለማስረከብ ይሠራል ብለዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ የሚሰጥ በወለድ መጠን ዝቅተኛ በሆነና በ30 ዓመታት የተራዘመ ክፍያ በተመጣጣኝ ዋጋ ለመካከለኛና ለዝቅተኛ ነዋሪዎች እንደሚተላለፍም ተገልጿል።
ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የዜጎችን የቤት ጥያቄ ለመፍታት የተለያዩ ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ የውጭ አልሚዎችን በመመልከትም በሪል ስቴት ከተሠማሩ የውጭ አልሚዎች መካከል ከ“ፕሮፐርቲ 2020” ኩባንያ ጋር ውል ተወስዷል ብለዋል።
የዘርፉን ልምድና አቅም የቀደመ ተሞክሮውን በመፈተሸ ፈቃድ መሰጠቱንም ገልጸዋል። ድርጅቱን ለአንድ ዓመት የማጥናት ሠራ ተሰርታል፤ የከተማ አስተዳደሩ መሬት አቅርበናል፤ ከቀረጥ ነጻ እቃ እንዲያስገባ ይደረጋል ብለዋል።
መሠረተ ልማትም እያማለን ነው፤ የረጅም ዓመት ልምዱን ተጠቅሞ በተያዘለት ጊዜ 100 ሺህ ቤቶችን ገንብቶ እንደሚያስረክብ እንጠብቃለን፤ ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ ሁሉንም ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።
በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ አንድ ሚሊዮን ቤቶችን ገንብቶ ለነዋሪዎች ለማዳረስ ከተማ አስተዳደሩ እየሠራ እንደሚገኝም ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል። የክፍያ ጊዜውና የዋጋ ጫናው ዝቅተኛ መሆኑ ትልቅ እድል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ስምምነቱ ከደቡብ አፍሪካ ጋር የቆየውን የዳበረ ግንኙነት ይበልጥ የሚያስተሳስር እና ትብብርን የሚያሳድግ እንደሆነ ምክትል ከንቲባዋ አስገንዝበዋል።
ናቲ ኤዲ ሞዲሴ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ የከተማ አስተዳደሩ ላደረገላቸው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በማመስገን በጥራትና በተቀመጠው ጊዜ ቤቶችን ገንብቶ ለማስረከብ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን- ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ